በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሕዝብን ሰላም በማናጋት ጥፋት ከመፈፀም ወጥተው የሰላም ጥሪን ሊቀበሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሕዝብን ሰላም በማናጋት ጥፋት ከመፈፀም ወጥተው የሰላም ጥሪን ሊቀበሉ ይገባል
ገንዳውኃ፣ ታሕሳስ 5/2018 (ኢዜአ):- በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሕዝብን ሰላም በማናጋት ጥፋት ከመፈፀም ወጥተው የሰላምን ጥሪን ሊቀበሉ ይገባል ሲሉ በአማራ ክልል የሰላምን ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ተናገሩ።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ የተሳሳተ መንገድ በመከተል ባደረስነው ጥፋት ተጸጽተንና ይቅርታ ጠይቀን የበደልነው ሕዝብ ለመካስ የሰላም አማራጭን ተቀብለን መጥተናል ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግስትና የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የዘላቂ ሰላም ስምምነት በቅርቡ መፈራረማቸውን ተከትሎ በየቀኑ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን እያስረከቡ እየገቡ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት በምዕራብ ጎንደር ዞን የሰላምን አማራጭ ተቀብለው የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች በገንዳ ውሃ ከተማ ከመንግስት አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ከተሳተፉት የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል አማረ ውበት፣ አረጋ አበበ እና በለጠ ሲራክ፤ በተሳሳተ መንገድ ጫካ በመግባት ጥፋት ፈፅመናል በዚህም ተጸጸተን ተመልሰናል ብለዋል።
በመሆኑም የተሳሳተ መንገድ በመከተል ባደረስነው ጥፋት ተጸጽተን የበደልነው ሕዝብ ለመካስ የሰላም አማራጭን ተቀብለን መጥተናል፤ የልማት አርበኛና የሰላም አምባሳደር ለመሆን ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል።
ችግርን በሰላማዊ ውይይትና ንግግር እንጂ በግጭት መፍታት እንደማይቻል በማመን የሰላም አማራጭ በመቀበል መምጣታቸውን ገልጸው፤ ሌሎች በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የህዝብን ሰላም በማናጋት ጥፋት ከመፈፀም ወጥተው የሰላምን ጥሪ ሊቀበሉ ይገባል ብለዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሰተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ፤ በዞኑና ክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል።
የሰላም አማራጭን በመከተል እድሉን የተጠቀሙትን ታጣቂዎች አመስግነው በጫካ የቀሩ ሀገርና ህዝብን በመበደል የታሪካዊ ጠላቶች መጠቀሚያ ከመሆን ተቆጥበው የተከፈተላቸውን የሰላም በር እንዲጠቀሙበት መክረዋል።
የሰላም አማራጭን ተቀብለው የተመለሱት የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት የበደሉትን ሕዝብ እየካሱ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የማመቻቸት ተግባር እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።
የዞኑ የሰላም ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ደረሰ አዱኛ በበኩላቸው፤ መንግስት ሰላምን ለማፅናት ባለው ቁርጠኝነት የሰላም በሩን ክፍት አድርጎ ታጣቂዎችን እየተቀበለ እና በዘላቂነት እያቋቋመ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በጫካ የቀሩ ታጣቂዎች የሰላሙን ጥሪ በመቀበል እንዲመጡ አሳስበው ፤ በማይቀበል የሽፍታ ሰብሰብ ላይ ጠንካራ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ504ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ቾምቤ ወርቁ፤ የቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ታጣቂዎች እድሉን መጠቀማቸው ጥሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ ባለመቀበል በጥፋት መንገድ በቀጠሉት ላይ ግን የጸጥታ ሃይሉ የተጠናከረ እርምጃ ይወስዳል ሲሉ አረጋግጠዋል።