በሶማሌ ክልል የሰፈነው ሰላም ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል-የህዝባዊ መድረክ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የሰፈነው ሰላም ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል-የህዝባዊ መድረክ ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 5/2018(ኢዜአ)፦በሶማሌ ክልል ከለውጡ በኋላ የሰፈነው ሰላም ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጉን በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ ህዝባዊ መድረክ ተሳታፊዎች ገለጹ።
"የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች "በሚል መሪ ሃሳብ በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ ህዝባዊ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ መንግሥት ተግባራዊ ባደረጋቸው አዳዲስ የአመራር ዕይታዎች ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በመሰረተ ልማት አቅርቦት ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው፤ የተገኙ ውጤቶችን ይበልጥ ለማጠናከር ከመንግሥት ጋር በትብብር እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
በስራ ዕድል ፈጠራ እና መስኖን ጨምሮ ለእርሻ ስራና አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላት የበለጠ በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፤ የሱማሌ ክልል ህዝብ ከመንግሥት ጋር በመሆን ያረጋገጠው ሰላም በርካታ ትሩፋቶችን ማስገኘቱን ጠቅሰዋል።
ህዝቡ የልማት ተጠቃሚ ሆኗል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሰላም ወሳኝ የልማት አካል ለመሆኑ የተገኘው ውጤት ማሳያ መሆኑን በአብነት ጠቅሰዋል።
በብልጽግና ፓርቲ አመራር ሰጪነት ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ምሳሌ የሚሆኑ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ገልጸው፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ የገበታ ለትውልድ እና ለሀገር ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
የገበታ ለትውልድ አካል የሆነውና በሶማሌ ክልል እየተገነባ ያለው ሸበሌ ሎጅ አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
ከመስኖ ልማት አኳያም የጎዴ መስኖ መሰረተ ልማት ተመርቆ ስራ ጀምሯል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህም ከ10 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ለመስኖ ልማት የሚያገለግሉ የውሃ ፓምፖች አቅርቦት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
መንግሥት ደረጃ በደረጃ የልማት ጥያቄዎችን እየመለሰ እንደሚሄድ አመልክተው፤ የተገኘውን ሰላም ቀጣይነት ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ህዝቡ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው፥ በአካባቢው የማዳበሪያና የነዳጅ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የመንገድ መሰረተ ልማቶች እየተሳለጡ መሆኑን አንስተዋል።
ቆራይና ሸበሌ አካባቢ በከፍተኛ ወጪ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ያሉት ኢንጂነር ሀብታሙ፤ መሰል ስራዎች መንግሥት የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች መሆናቸውን ተናግረዋል።
አካባቢው የጉባ ብስራቶች አካል የሆኑ ፕሮጀክቶች የሚተገበሩበት በመሆኑ ፕሮጀክቶቹ ከሚያመጡት ዕድል በሰፊው ለመጠቀም ባለድርሻ አካላት ከህዝቡ ጋር ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን ከለውጡ በፊት በክልሉ የተረጋጋ ሰላም እንዳልነበር አስታውሰው፤ ከለውጡ ወዲህ በተከናወኑ ተግባራት በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ ይፋ ካደረጓቸው የጉባ ብስራቶች መካከል በክልሉ ውስጥ የሚገነቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
አሁን ላይ በክልሉ ሰላም፣በመረጋገጡ ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በተለይም በጎዴ አካባቢ ግዙፍ የልማት ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡