ቀጥታ፡

ኪነ-ጥበብ በተደመረ አቅም የኢትዮጵያን ከፍታ እንዲያረጋግጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 5/2018 (ኢዜአ)፡-ኪነ-ጥበብ ዘርፉ በተደመረ አቅም የኢትዮጵያን ከፍታ እንዲያረጋግጥ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ገለጹ።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በተዘጋጁ የጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ፣ሌሎች የህግ ማእቀፎች እና በጸደቁ የአሰራር መመሪያዎች ላይ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በዚሁ ወቅት ጥበብ ባህላዊ እና ዘመናዊ መልክ እንዳለው ገልጸዋል።

እንዲሁም ስነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊ እና ሀገራዊ ጥቅሞች እንዳሉት ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ በርካታ የጥበብ ስራዎች ቢሰሩም ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲ እንዳልነበረ አስታውቀዋል።

ባለፉት ሶስት ወራት ምሁራን፣ ባለድርሻ አካላት እና የዘርፉን ባለሙያዎች ያካተተ የጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

ረቂቅ ፖሊሲው የኪነ-ጥበብ ዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ፣ ለዘርፉ ተዋንያን እውቅና የሚሰጥ እና የዘርፉ እድገት የሚተለምበት መሆኑን ተናግረዋል።

ረቂቅ ፖሊሲውን የሚያዳብሩ የተለያዩ ግብዓቶች ከተሰበሰቡ በኋላ በሚመለከተው አካል  እንደሚጸድቅ አመላክተዋል።

በጥበባት ካውንስል ምስረታ ላይ ውይይት መደረጉን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም ከዚህ ቀደም በዘርፉ ያልነበረ አደረጃጀት መሆኑን ጠቁመዋል።

አደረጃጀቱ ከፍተኛ አቅምና ሰፊ አድማስ እንዳለው ጠቁመው በተለይም ከያንያን ለሀገራቸው ትልቅ ስራ የሚሰሩበት እና ከመሪዎች ጋር እየተገናኙ ውይይት የሚያደርጉበት መሆኑን አመላክተዋል።

የተበታተነውን አካሄድ ወደ ተደመረ ጉልበት በማምጣት ኢትዮጵያን ከፍ አድርጎ ሊያወጣ የሚችል መሆኑን አመላክተዋል።

ከማህበራት አደረጃጀት አሰራር ጋር የተያያዘ ውይይት መደረጉን ገልጸው ጠንካራ ማህበራትን ለማቋቋም መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት ለጥበብ ዘርፍ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ስትራቴጂክ በሆነ አግባብ ጥበብን እየደገፈ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በፖሊሲው የተነሱ የእውቅና፣ የመሰረተ ልማት፣ የትምህርት፣ የአቅም ግንባታ እንዲሁም ለሌሎች አበይት ጉዳዮች መንግስት ቀድሞ ተግባራዊ ያደረጋቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ዘርፉ  የተደመረ፣ጉልበት ያለውና ኢትዮጵያን ከፍ የሚያረግ እንዲሆን መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም