ለሕዝብ ዘላቂ ሰላምና የልማት ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው-የደብረ ብርሃን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሕዝብ ዘላቂ ሰላምና የልማት ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው-የደብረ ብርሃን ነዋሪዎች
ደብረብርሃን፤ታሕሳስ 5/2018(ኢዜአ)፡-ለሕዝብ ዘላቂ ሰላምና የልማት ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች በአማራ ክልል ለሰላም አማራጭ ትኩረት በመስጠት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት አድንቀዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ሀይለ ስላሴ ጌታነህ ፣ አቶ ሸዋለዓለም ግዛቸው ፣ አቶ ሙሉጌታ መንገሻ እና አቶ ሙላት ሀይሉ በለውጡ ዓመታት በከተሞች ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፤በግብርና እና በቱሪዝም ዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትም እመርታዊ ውጤት የመጣባቸው መሆኑን አንስተዋል።
ለሕዝብ ዘላቂ ሰላምና የልማት ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፥ በሕረተሰቡ ተሳትፎ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
መንግስት ከሕብረተሰቡ ጋር የሚያደርገው ውይይት እያደገ በመምጣቱ ችግሮችን ለመፍታት ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል።
አልፎ አልፎ የሚስተዋለው የመብራት ፣የውሃና የመንገድ መሰረተ ልማት ያለመሟላት ችግር እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።
የዋጋ ንረትን ከመከላከልና በሁሉም አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም በመፍጠር ረገድ እየተከናወነ ያለው ውጤታማ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተዋል።
ከግጭት ይልቅ ችግርን በሰላማዊ መንገድ ለዘላቂ መፍትሄ መስራት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት የመድረኩ ታዳሚዎች በዚህ ረገድ መንግስት በትኩረት መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጫካ የገቡትን መክረን አስተምረን የመመለስ ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የበርካታ ባለሃብቶች መዳረሻ የሆነችው ደብረ ብርሃን ከተማና አካባቢው ልማቷ ተጠናክሮ ሰላም ተጠብቆ እንዲዘልቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንዳመለከቱት፤ በከተማው የነዋሪዎችን ጥያቄ መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክረው ቀጥለዋል።
በከተማው የአገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን፣የኮሪደር ልማት፣ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት፣የመንገድ መሰረተ ልማትን ተደራሽ የማድረግና የገበያ ማረጋጋት ስራም እንዲሁ።
ከነዋሪዎች የተነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንደሚያገኙ አረጋግጠዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማስረሻ በላቸው፤ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ሕዝቡ ያለውን አጋርነትና ቁርጠኝነት አድንቀው፤ በዚህ ጉዳይ መንግስትም ዋነኛ ትኩረቱ ሆኖ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ያሉ እምቅ ሃብቶችን በማልማት ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣትና የዋጋ ንረትን የመከላከል ስራም ትኩረት የሚደረግበት መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ የመንግስት ጥረት ውስጥ የሕዝቡ እገዛና ትብብር አስፈላጊ በመሆኑ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)፤ለሀገር እድገትና ማንሰራራት በጋራ ተግቶ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን በመተግበር ደብረ ብርሃን ጥሩ ማሳያ መሆኗን አንስተው፤ በሁሉም መስኮች የተያዙ የልማት እቅዶችን በማሳካት ከድህነት መውጣት ይገባናል ብለዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ሰላምን የማፅናት፣የልማት ስራዎችን የማስቀጠልና የገበያ ማረጋጋትን ተግባር በተቀናጀ አግባብ እንደሚቀጥልና ሕብረተሰቡም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጠል ጠይቀዋል።
''የጉባ ብስራቶች፣የመደመር መንግስት ትሩፋቶች'' በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ከተሞች ትናንት ተመሳሳይ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸው ይታወቃል።