ቀጥታ፡

በመንግስት የተጀመሩ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫና የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ

ሚዛን አማን፣ ታኅሣሥ 5/2018 (ኢዜአ)፡- በመንግስት የተጀመሩ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫና የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

"የጉባ ብሥራቶች፤ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በሚዛን አማን ከተማ ዛሬ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሬሳ (ዶ/ር) እና የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተገኝተዋል።


 

የመድረኩ ተሳታፊዎች መንግሥት እንደ ሀገር ብሎም በአካባቢያቸው በርካታ የልማት ውጤቶችን በማስመዝገብ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አንስተዋል።

በተለይ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት እንዲሁም በሌሎች የልማት መስኮች በተከናወኑ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ በመሆናቸው ልማቱን ለማጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በፌዴራል መንግሥት በከተማ አስተዳደሩ እየተገነቡ ያሉ የአየር ማረፊያና የደንቢ ሎጅ ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ኢኮቱሪዝም የሚያሳድጉ በመሆናቸው አመስግነው፣ በቀጣይም የማህበራዊ አገልግሎትና የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ንጉሤ ፈይሳ ከሚዛን ዲማ የተዘረጋው የአስፋልት መንገድ በመበላሸቱ ህብረተሰቡን ለእንግልት እየዳረገ መሆኑን አንስተው፣ በሚዛን አማን ከተማ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ችግር በመኖሩም እንዲሰራላቸው ጠይቀዋል።  


 

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ቲቺንግ ሆስፒታል ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ክፍተት እንዳለ ያነሱት ወይዘሮ ጥሩዬ ከበደ፤ "በሆስፒታሉ የአልጋና የመድኃኒት እጥረት በመኖሩ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የጤና መድኅን አባል ብንሆንም ተገቢውን አገልግሎት እያገኘን አይደለም" ብለዋል።

በሆስፒታሉ እየታየ ያለውን የሥራ ጫና ለመቀነስ በከተማዋ ተጨማሪ ሆስፒታል ቢገነባልን ሲሉ የጠየቁት ደግም  ወይዘሮ አስመረት ቸሬ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።

አካባቢው ለግብርና ሥራ ምቹ በመሆኑ የተለያዩ የግብርና ምርቶች ቢመረቱም እሴት ጨምሮ ለማምረት የሚያስችል ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የለም ያሉት ደግሞ አቶ ብርሃኑ ሽፈራው የተባሉ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ናቸው።

በአካባቢው የአግሮ ፕሮሰሲንግ እና ሌሎች ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ቢስፋፉ አርሶ አደሩን በተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ፣  የአካባቢውን ዕድገት ለማፋጠንና ለወጣቶችም የሥራ ዕድል ጠቀሜታ ስላለው መንግስት ትኩረት ቢሰጠው ሲሉ ጠይቀዋል።

መንግስት የከተማዋን የነዋሪዎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑም የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።


 

የውይይት መድረኩን የመሩት በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሬሳ (ዶ/ር) አካባቢው በግብርና ምርት ሌሎች አካባቢዎችን ጭምር መመገብ የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳለው አንስተዋል። 

ይሁንና ከምርቱ ህብረተሰቡ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ እንዳይሆን እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በመንግስት ሕዝብን ያሳተፈ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ከራስ ባለፈ የአካባቢውን ባለሀብት በማቀናጀት ወደ ኢንዱስትሪ ለማስገባት በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረትም ይሰራል ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡

መንግሥት ሕዝብን አዳምጦ ለተነሱ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት የሚያደርገውን ጥረት ያጠናክራል ያሉት ቢቂላ (ዶ/ር)፤ ከህብረተሰቡ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ኢትዮጵያን ከፍ እናደርጋታለን ብለዋል።


 

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ ሕዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች በመያዝ ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ ይሰራል ብለዋል።

በክልሉ የተጀመሩ የላቦራቶሪ ማዕከል ግንባታና በሂደት ላይ የሚገኙ የደም ባንክና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች የሕዝብ እንግልትን መቀነስ ስለሚያስችሉ ተከታትለው እንደሚያስፈጽሙ አረጋግጠዋል።

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሰሎሞን ሌዊ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የከተማ መሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትንም ከዋቻ-ሚዛን-ዲማ ያለውን የመንገድ ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው የፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም