በክልሉ የተመዘገቡ የልማት ስራዎች የበለጠ እንዲጠናከሩ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻችንን እንወጣለን -- የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተመዘገቡ የልማት ስራዎች የበለጠ እንዲጠናከሩ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻችንን እንወጣለን -- የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች
ጅግጅጋ፤ ታህሳስ 5/2018(ኢዜአ)፦ በክልሉ የተመዘገቡ የልማት ስራዎች የበለጠ እንዲጠናከሩ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
"የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው ዕለት በጅግጅጋ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
ከጅግጅጋ ከተማና አካባቢው የመጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች ባነሱት አስተያየት በክልሉ በተለይም ከለውጡ ወዲህ የተመዘገቡ የልማት ስራዎች የተሻለ ውጤት የተመዘገበባቸው መሆኑን አንስተው፤ የበለጠ እንዲጠናከሩ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ቺፍ አቅል አህመድ ሁሴን፤ ባለፉት ዓመታት በርካታ የልማት ስኬቶች መመዝገባቸውን ተመልክተናል ብለዋል።
በቀጣይም እነዚህ ውጤታማ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና የህዘቡ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ድጋፋችን ይቀጥላል ሲሉም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ከዚህ በፊት ተጠይቀው ምላሽ ያላገኙ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ጨምሮ በጅግጅጋ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኘው መንገድ ፈጥኖ መጠናቀቅ እንዳለበት አንስተዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ዑመር ሀሰን ሂርስ፤ በከተማውና አጠቃላይ በክልሉ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች መንግስትን የሚያስመሰግኑ መሆናቸውን አንስተዋል።
የተከናወኑት የልማት ስራዎች በበጎ መልኩ የሚገለጹ ቢሆኑም አሁንም በከተማው የንጹህ መጠጥ ውኃ እጥረት መኖሩን ጠቁመው መንግሥት የከተማውን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በክልሉ ለተከናወኑ በርካታ የልማት ሥራዎች ህዝቡ ሰላሙን ከመጠበቅ ጀምሮ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ ሊቀ ካህናት ኢዮብ ወንድሙ ናቸው።
በጅግጅጋ ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸው በከተማው የሚስተዋለው የመንገድ እና የመብራት ችግሮችም መፍትሄ እያገኙ መሆኑን አንስተዋል።
ሌላኛዋ የውይይት መድረኩ ተሳታፊ ሉል ሼኽ አብዲ፣ መንግሥት ለሥራ ፈጠራ የሰጠው ትኩረት የበለጠ መጠናከር እንዲችል ድጋፋችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፤ የመደመር መንግሥት በሁሉም አካባቢ ያሉትን አቅሞች ለይቶ በማልማት ለህዝቡ ተጠቃሚነት እየተጋ ይገኛል ብለዋል።
በለውጡ ዓመታት በተሰራው ስራ ስንዴ ከውጭ ማስገባት ማቆም መቻሉን ለአብነት ያነሱት አቶ ጥላሁን በሁሉም ዘርፎች ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
የሶማሌ ክልል እምቅ የፈጥሮ ሃብት ያለው ክልል በመሆኑ መንግስት ለአካባቢው ሁለንተናዊ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በጅግጅጋ ከተማ አስተዳደርም ከህዝቡ የተነሱ የውሃ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እና የመብራት የተመለከቱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋልም ብለዋል።
የሀረሪ ብሄራዊ ጉባኤ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም፤ መንግስት በሁሉም አካባቢዎች ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ለማረጋገጥ ባደረገው ጥረት ምሳሌ የሚሆኑ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
የተገኘውን ስኬት ለማስቀጥል ህዝቡ ከመንግስት ጎን ተሳልፎ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በጅግጂጋ ከተማ የተጀመሩ ስራዎችን የበለጠ በማሳደግ ከተማዋን የንግድ ማዕከል ለማድረግ የክልሉ መንግስት በቁርጠኝነት ይሰራል ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሌ ናቸው።