ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ እና የሀገርን ብልፅግና እውን የሚያደርጉ ናቸው - ነዋሪዎች

ቦንጋ ፣ ታህሳስ  5/2018 (ኢዜአ)፡- በለውጡ ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ እና የሀገርን ብልፅግና እውን የሚያደርጉ ናቸው ሲሉ የቦንጋ ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎች  ተናገሩ።

"የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ በቦንጋ ከተማ ህዝባዊ ውይይት ተካሄዷል ።

የውይይት መድረኩ ላይ ከቦንጋ ከተማና አካባቢዋ የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን ከለውጡ ዓመታት ወዲህ በተመዘገቡ የልማት ውጤቶችና በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ተሳታፊዎቹ ሀሳቦችን አንስተዋል።


 

ከተሳታፊዎቹ መካከል የቦንጋ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አባይነሽ ከበደ እንደገለፁት፤ ብልፅግና አሳታፊና ህዝባዊ ፓርቲ በመሆኑ ለዓመታት ለቆየው ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ብዙ ትሩፋቶችን አግኝተናል።

የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ከብዙ ዓመታት መጓተት በኋላ ወደ ስራ መግባቱ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ እየተሰራ ያለው ሰው ተኮር ተግባር እንዲሁም የሌማት ትሩፋትና ሌሎችም ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።

የለውጡ መንግስት በሁሉም ዘርፎች ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረገና የሀገርን ብልፅግና እውን የሚያደርጉ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ያነሱት ደግሞ ሌላኛው የቦንጋ ከተማ ነዋሪ አቶ አለማየሁ ከበደ ናቸው።

በዚህም እንደሀገር የሚቀረፁ ኢንሼቲቮች የክልሉንና የከተማውን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ በኮሪደር ልማትና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተገኙ ውጤቶችን አንስተዋል።

የኑሮ ውድነት ተፅዕኖን ለመቀነስ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በከተማው የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪና በየተቋማቱ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥና ብልሹ አሰራሮችን ለማረም የተጠናከር ስራ ስራ መሰራት አለበት ብለዋል።

አየለ ወልደ ገብርኤል የተባሉ አስተያየት ሰጪ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከኢትዮጵያም አልፎ ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆኑ በርካታ የልማት ድሎች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል። 

የካፋ ህዝብ ለሰላም የሚሰጠው ቦታ ትልቅ መሆኑን አንስተው በቀጣይም ይህን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ በሀገር ደረጃ ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።


 

የውይይት መድረኩን የመሩት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ መንግስት በአካባቢው ለረጅም ጊዜ የቆዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመመለስ እዳን ወደ ምንዳ እየቀየረ መሆኑን አንስተዋል። 

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በማዕድንና በሌሎችም ዘርፎች በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል። 

በአንድነትና በህብረት ለአንድ ሀገር ከቆምን የጉባ ብስራቶችን በማሳካት የኢትዮጵያን ማንሰራራት ከዳር ማድረስና ከሂደቱም ሁላችንም ተጠቃሚ መሆን እንችላለን ብለዋል።

ከነዋሪዎቹም በመልካም አስተዳደር፣ በልማትና በሰላም ዙሪያ የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያኙ በፌደራል፣ በክልል፣ በዞንና በወረዳ እንዲሁም በቀበሌ ደረጃ ምላሽ የሚያገኙ መሆኑንም አስረድተዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ከህብረተሰቡ የተነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለቅሞ በመያዝ ምላሽ እንዲያገኙ የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አንስተው፣ በዚህም በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውንና ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። 


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ፤ ከለውጡ ወዲህ በመንግስት እና በህዝቡ ሰፊ ተሳትፎ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

መንግስት ችግሮችን ወደ ዕድል በመቀየርና የሀገራችንን ፀጋ በመለየት በሁሉም መስኮች እመርታዊ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏልም ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም