በሐረሪ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ ነው - የሐረር ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ ነው - የሐረር ከተማ ነዋሪዎች
ሐረር፣ታህሳስ 5/2018(ኢዜአ):-በሐረሪ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ መሆኑን የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
"የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ በሐረሪ ክልል ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉት የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደተናገሩት፥ በክልሉ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የህዝቡን ጥያቄ የመለሱ መሆኑን አንስተዋል።
ከለውጡ ዓመታት ወዲህ የተከናወኑ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ መሆኑን አንስተው፥ በቀጣይም ለላቀ ስኬት ከመንግስት ጎን በመቆም እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ ጀማል ከቤ፤ በክልሉ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ገቢን አሟጦ የመሰብሰብ ስራን በማጠናከር ረገድ ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበት አንስተው፥ በሀገር አቀፍ ደረጃም የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እየተሰራ ያለው ስራ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ከክልሉ ከፍተኛ አመራር እስከ ታችኛው እርከን ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር የተከናወኑ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል ህዝብንም ተጠቃሚ አድርገዋል ብለዋል።
እንደ ሀገርና በክልሉ እየተከናወኑና እየተመዘገቡ የሚገኙት የልማት ስራዎችን ለማደናቀፍ ፀረ ልማት ሃይሎች የሚያከናውኑትን ሴራ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር ሆነው እንደሚከላከሉም ተናግረዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሙሊካ ዘካርያ፤ ዓለም አቀፉን የጁገል ቅርስ መልሶ በመልማቱ ቅርሱ ተደቅኖበት ከነበረው አደጋ ከመታደግ ባሻገር ለነዋሪውና ጎብኚዎች ፅዱና ምቹ ማድረግ መቻሉንና የመደመር እሳቤን እውን ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በቀጣይም የክልሉ መንግስት የሚያከናውናቸውን የልማት ስራዎች በመደገፍ በክልሉ ሁለንተናዊ ለውጥን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ የበኩላቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡ ገልፀዋል።
"አባት እናቶቻችን ያላዩትን ልማት ማየት ችያለሁ፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ" ያሉት ደግሞ ሼህ መሐመድ ጋቱር ናቸው።
በውጪ ሀገር ያየሁትን በሀገሬ በማየቴ ደስተኛ ነኝ ሲሉም ተናግረዋል።
በቀጣይም ከጠቅላይ ሚኒስትራችንና ከፕሬዝዳንታችን ጋር ሆነን እንሰራለን፤ ለልጆቻችንም የምናስተላልፈውን ውብ ሀገር እንገነባለን ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባልና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በክልሉ አመራሩና ህዝቡ ተቀናጅተው ውጤታማ ስራ ማከናወናቸውን አንስተዋል።
በክልሉ ለበርካታ ዓመታት ተደራርበው የቆዩ የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ምላሽ ለመስጠት የተከናወኑ የልማት ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸው፥ ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የተነሱ ጥያቄና አስተያየቶችን መሰረት በማድረግ በሂደት ምላሽ እንዲያገኙ በየደረጃው ያለው የመንግስት አካል ከህዝቡ ጋር የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባልና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፤ ከለውጡ ወዲህ በሐረር ከተማ የተሰሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ከተማዋን የመደመር መንግስትና የብልፅግና ተምሳሌት ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ የተሰሩ የልማት ስራዎች የሐረርን ከፍታ ያረጋገጡ በመሆናቸው የተሰሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
በመደመር እሳቤ የባህር በር ጥያቄያችንን እውን እናደርጋለን ያሉት ሚኒስትሯ፤ ማህበረሰቡም አንድነቱን ይበልጥ በማጎልበት በጋራ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሱልጣን አብዱሰላም፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመርና ሌሎችም የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል።