ረቂቅ ፖሊሲው የኪነጥበብ ዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ነው - ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ - ኢዜአ አማርኛ
ረቂቅ ፖሊሲው የኪነጥበብ ዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ነው - ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 5/2018(ኢዜአ)፦የጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ የኪነጥበብ ዘርፉን በውጤታማነት በመምራት ተወዳዳሪነቱን የሚያሳድግ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ገለጹ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲና ሌሎች የህግ ማእቀፎች እንዲሁም በጸደቁ የአሰራር መመሪያዎች ላይ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በዚሁ ወቅት ጥበብ ባህላዊ እና ዘመናዊ መልክ እንዳለው ገልጸዋል።
እንዲሁም ስነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊ እና ሀገራዊ ጥቅሞች እንዳሉት ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ በርካታ የጥበብ ስራዎች ቢሰሩም ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲ እንዳልነበረ አስታውቀዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት ምሁራን፣ ባለድርሻ አካላት እና የዘርፉን ባለሙያዎች ያካተተ የጥበባት እና ፈጠራ ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።
ረቂቅ ፖሊሲው የኪነ-ጥበብ ዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ፣ ለዘርፉ ተዋንያን እውቅና የሚሰጥ እና የዘርፉ እድገት የሚተለምበት መሆኑን ተናግረዋል።
ረቂቅ ፖሊሲውን የሚያዳብሩ የተለያዩ ግብዓቶች ከተሰበሰቡ በኋላ በሚመለከተው አካል እንደሚጸድቅ አመላክተዋል።
በውይይት መድረኩ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻህፍት ዋና ዳይሬክተር ሰርጸ ፍሬስብሀት፣ አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣የክልል የባህልና ስፖርት ቢሮ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።