ቀጥታ፡

በዚህ ዓመት በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና በተፋሰስ ልማት 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ይለማል-የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 5/2018(ኢዜአ)፦ በዚህ ዓመት በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና በተፋሰስ ልማት 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሔክታር መሬት እንደሚለማ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈጻሚ ፋኖሴ መኮንን፤ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በማህበረሰቡ ዘንድ ባህል እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡

በየዓመቱ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች በህብረተሰብ ንቅናቄ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ፤ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ለምነት እንዲጨምርና ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እያደረገ ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ወጣቶች ተደራጅተው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን እንዲያመርቱ በማስቻል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥር ወር ላይ በይፋ እንደሚጀመር ጠቅሰው፥ ለዚህም የዝግጅት ስራው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት በ21 ሺህ ተፋሰሶች በሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሔክታር መሬት እንደሚለማ አስረድተዋል፡፡

የተፈጥሮ ሃብት ስራ የተፈጥሮ ሚዛንን በመጠበቅ ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በንቅናቄው ወጥቶ መስራት እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።

በሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በድርቅ እና በአካባቢ መራቆት የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ይደረጋል ብለዋል።

በየዓመቱ በህዝብ ንቅናቄ በሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በአማካይ ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ህብረተሰቡ በአማካይ በየዓመቱ ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጊዜ፣ ጉልበትና ሀብት አስተዋጽኦ የሚያደርግበት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም