የወጣቶች አደረጃጀቶች በበጎ ፍቃድ ደም ከመለገስ ባሻገር የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ላይ ተሳትፎአቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የወጣቶች አደረጃጀቶች በበጎ ፍቃድ ደም ከመለገስ ባሻገር የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ላይ ተሳትፎአቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ
አዳማ፤ ታህሳስ 5/2018(ኢዜአ)፡-የወጣት አደረጃጀቶች በበጎ ፍቃድ ደም ከመለገስ ባሻገር የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ተሳትፎአቸውን እንዲያጠናክሩ የኢትዮጵያ ደምና ሕብረህዋስ አገልግሎት ጠየቀ።
አገልግሎቱ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ደም ለጋሽ ማህበር ጋር ባለፉት አምስት ወራት ያከናወናቸውን የደም አሰባሰብ ሂደትና የቀጣይ በጋ ወራት የደም አሰባሰብ ዕቅድ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ አካሄደዋል ።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው እንደገለፁት በበጀት ዓመቱ 550 ሺህ ዩኒቲ ደም ለመሰብሰብ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን ጨምሮ ተማሪዎች፣ የኃይማኖት ተቋማትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።
ለተግባራዊነቱም የማህበረሰቡን የደም የመለገስ ባህል ለማሳደግ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶችና ትምህርት ቤቶች በማሳተፍ ባለፉት አምስት ወራት 202 ሺህ ዩኒቲ ደም ተሰብስቧል ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ ስራውን በበጋ ወራት ለማስቀጠል የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች ከሚያደርጉት የበጎ ፍቃድ የደም ልገሳ ባሻገር ህብረተሰቡን በማስገንዘብ ረገድ ያላቸውን ሚና እንዲያጠናክሩ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ጂማ እና ጂግጅጋን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ቋሚ ደምለጋሽ አባላት ማፍራቱን አንስተዋል።
ወጣቶቹ በበጎ ፈቃድ በሚለግሱት ደም ሌሎች እንዲሳተፉ የንቅናቄ ተግባር ላይ በመሳተፍ ህይወት እያዳኑ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ በበኩላቸው የመዲናዋን የጤና ተቋማት የደም ፍላጎት ለማሟላት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በደም እጦት ምክንያት የሚሞቱ እናቶችና ዜጎችን ቁጥር ዜሮ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ደም ለጋሽ ማህበር አስተባባሪ ወጣት ነቢዩ ሙሰማ በበኩሉ ማህበሩ በደም እጦት የሚሞቱ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ አባላቱን በማስተባበር ደም እያሰባሰበ ይገኛል ብለዋል።
ማህበሩ በየሶስት ወሩ በቋሚነት ከሚሰበሰበው ደም በተጨማሪ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ደም እንዲለግሱ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ባለፉት አምስት ወራት ማህበሩ ሲያከናውን የቆየውን የደም ልገሳ በበጋ ወራት ለማጠናከር ማቀዱን ጠቁመዋል።