ቀጥታ፡

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመሰማራት ተኪ ምርት ላይ በማተኮራችን ውጤታማ ሆነናል-ማህበራት

ወልቂጤ፤ታህሳስ 5/2018 (ኢዜአ):-በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመሰማራት ተኪ ምርት ላይ በማተኮራቸው ውጤታማ መሆናቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራት ተናገሩ።

የክልሉ ስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ በበኩሉ በተለያዩ የስራ ዘርፎች የሚሰማሩ ዜጎች ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፆ፥በተያዘው ዓመት ለ400 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጠር ይሆናል ብሏል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተደራጁ ማህበራት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በማምረት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በሆሳዕና ከተማ የሚገኘው የዋቻሞ ኢንተርፕራይዝ ተወካይ ወይዘሪት ምስጋና ዝግዴ ከዓመት በፊት ለ5 ተደራጅተው ቡና በዘመናዊ ማሽን በመፍጨትና ቆልቶ በማሸግ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ተናግራለች።

መንግስት ወደዚህ ስራ እንዲገቡ ክህሎታቸውን ከማሳደግ ባለፈ የመስሪያ ቦታ እንዳመቻቸላቸው ገልፃ፥ የቡና ምርቱን ከሃገር አልፎ ወደ ውጭ በመላክ የገበያ ትስስራቸው መስፋቱን አንስታለች።

በመቶ ሺህ ብር የጀመሩት ካፒታል አሁን ላይ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን ገልጻ፥በዚህም ኢኮኖሚያቸውን በማሳደግ ለ30 ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግራለች።

በቡታጅራ ከተማ የሚገኘው የአግኖት የሳሙናና እና ዲተርጀንት ማምረቻ ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ አይዳ ወልጫፎ በበኩላቸው፥ ሶስት ሆነው የጀመሩት ስራ ውጤታማ ሆኖ ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ምርቱን ለማምረት ሁሉም ግብአቶች በሃገር ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸው፥በዚህም ከውጭ ይገቡ የነበሩ ሳሙናና የንፅህና መጠበቂያ ዲተርጀንቶችን በሃገር ውስጥ ማምረት መቻላቸውን ተናግረዋል።

የተፈጠረው የገበያ ትስስር ውጤታማ እንዳደረጋቸው እና በስፋት ለመስራት እያነሳሳቸው መሆኑን አመልክተዋል።

መንግስት የመነሻ ብድርና የመስሪያ ቦታ እንዲሁም የሊዝ ማሽን በማቅረቡ ወደ ስራ መግባታቸውን የገለፁት ደግሞ በክልሉ በመስቃን ወረዳ በቤትና በቢሮ ዕቃዎች ምርት ላይ የተሰማሩት አቶ ማረኝ ደመቀ ናቸው።

በዚህም ከውጭ ይገቡ የነበሩ የቤትና የቢሮ መገልገያ የእንጨት ውጤቶችን በማምረት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ፥ በክልሉ ክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት በማድረግ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ ተኪ ምርቶች ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ የተገኘውን ውጤት የማስቀጠል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ ዘርፉ ለበርካቶች የስራ እድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ለ400 ሺህ ስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጠር የገለጹት አቶ ሙስጠፋ፥ ባለፉት ወራት ውስጥ ከ193 ሺህ 104 ዜጎች በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልፀዋል።

የክህሎት ስልጠና፣የገበያ ትስስር መፍጠር፣ የመስሪያና መሸጫ ቦታዎችን ማመቻቸት እንዲሁም ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም