ቀጥታ፡

በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል እና አገልግሎቶቹን የማስፋት ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 5/2018(ኢዜአ)፡- መሶብ የአንድ ማዕከልንና የሚሰጡ የአገልግሎት ዓይነቶችን ለማስፋት እየተሠራ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሠመረ ጂራታ(ኢ/ር) ተናገሩ።

ለዜጎች የሚሰጥ አገልግሎት ከቅሬታ የጸዳ፣ ጊዜና ወጭ ቆጣቢ፣ ፍትሐዊ ብሎም ተደራሽ እንዲሆን ማስቻል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ዓላማ መሆኑን አስገንዝበዋል።

እንደ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአምሥት የክልል እና በሦስት የፌደራል ተቋማት በ33 ዘርፎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

እስካሁንም ከ6ሺህ 300 በላይ ተገልጋዮች አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

በቀጣይ ወደ ማዕከሉ የሚገቡ ተቋማትና አገልግሎቶችን ቁጥር የማስፋት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት ተጨማሪ አንድ የፌደራል እና ሦስት የክልል ተቋማት ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል መግባት የሚያስችላቸውን ሥራ እያከናወኑ ነው ብለዋል።

ይህን ተከትሎም በአጭር ጊዜ አምሥት ተጨማሪ አገልግሎቶች ወደ ማዕከሉ እንደሚገቡ አመላክተዋል።

በሌላ በኩል በአሶሳ ከተማ አሥተዳደር ደረጃ መሶብ የአንድ ማዕከል እንዲኖር እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም