ቀጥታ፡

ለቡና ልማት፣ ጥራትና ግብይት የተሰጠው ትኩረት አምራቹን ተጠቃሚ በማድረግ ለሀገርም የውጭ ምንዛሪ ገቢ እያሳደገ ነው

አዶላ፤  ታህሳስ 5.2018(ኢዜአ) ፡-  ለቡና ልማት፣ ጥራትና ግብይት የሰጠው ትኩረት አምራቹን ተጠቃሚ በማድረግ  ለሀገርም የውጪ ምንዛሪ ገቢ እያሳደገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።

በጉጂ ዞን አዶላ ወዩ ዙሪያ ወረዳ ቢርቢርሳ ቢሉ ቀበሌ የተቋቋመው የቡና ጣዕም ቅምሻ ማዕከል የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)፣ ባለፉት ዓመታት መንግስት ለቡና ልማት፣ ጥራትና ግብይት የሰጠው ትኩረት አምራቹን ተጠቃሚ እያደረገ ለሀገርም የውጭ ምንዛሪ ገቢ እያሳደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሻሻሉ የቡና ችግኝ ዝርያን በመጠቀም የቡና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች በተከታታይ ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል።


 

የቡና ምርትን በጥራት  ለማሳደግ አምራች አርሶ አደሮችን፣ ነጋዴዎችንና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የግንዛቤ ማሳደግ ስራዎች በሁሉም አካባቢዎች መሰራቱን አውስተዋል።

በዚህም መሰረት ባለፈው ዓመት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የቀረበ የቡና ምርት ማሳደግ መቻሉን ገልጸው፤  ዘንድሮም የተሻለ ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል ብለዋል።


 

የኦሮሚያ ክልልም የቡና ምርት በስፋት ከሚሰበስብባቸው የሀገሪቱ  አካባቢዎች ትልቁ መሆኑን ጠቅሰው፤  በተለይም የጉጂ ቡና በተፈጥሮ ጣዕምና ጥራቱ ከሀገር አልፎ በአለም ገበያ ይበልጥ አዋጭ እየሆነ  መምጣቱን ተናግረዋል።

በዞኑ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የቡና ጣዕም መቅመሻ ማዕከልም በአካባቢው የሚመመረተው ቡና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለገበያ እንዲቀርብ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ፣ በክልሉ የቡና ምርታማነትን የማሳደግ እና ጥራትን የማስጠበቅ ስራዎች ውጤታማ እየሆኑ መጥተዋል ብለዋል።

ከክልሉ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የቡና ጣዕም ቅምሻ ማዕከሉ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነጋሽ ቡላላ በበኩላቸው ከዞኑ ባለፈው ዓመት ከ70 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን አስታውሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከዞኑ ከ120 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን ጠቅሰው፤ በዞኑ ከ160 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የቡና ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚእንደሆኑና ከ473 ሺህ ሄክታር በላይ በቡና ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት መኖሩን አመላክተዋል፡፡


 

በዞኑ የተቋቋመው የቡና ጥራትና ጣዕም ቅምሻ ማዕከል አምራቹን ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ አዶላ ሬዴ ወረዳ የአንፈራራ ቀበሌ ቡና አምራች አቶ ታሪኩ መራሚ፣ ማዕከሉ ቡናን ይበልጥ በጥራት ለማልማት  የሚያበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ልማቱን በማስፋፋት ሰርተን ለመለዋጥ ብሎም ለሀገራችንም የውጭ ምንዛሪ  ለማስገኘት ህግና ስርዓትን አክብረን እንድንሰራ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ለተፈጥሮ ቡና ጣዕም ጥራትና ደረጃ መሻሻል ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርት አሰባሰብ በግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ እያገኙ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም