በባሕርዳር ከተማ 24 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በባሕርዳር ከተማ 24 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ
ባሕርዳር፤ ታህሳስ 5/2018(ኢዜአ)፡- በባሕርዳር ከተማ ባለፉት አምስት ወራት 24 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 184 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የአስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ብርሃን ንጉሴ፤ የባሕርዳር ከተማን ተመራጭ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ ባለፉት አምስት ወራት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስረድተዋል።
በዚህም 24 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 184 ባለሃብቶች አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ሆቴልና ቱሪዝምን ጨምሮ በሌሎችም መስኮች ለመሰማራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ጠይቀው እንደተሰጣቸው አስታወቀዋል።
ባለሀብቶቹ ወደ ግንባታና ማምረት ስራ ሲሸጋገሩ ተኪና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ከማምረት በተጨማሪ ለበርካታ ወገኖች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም ቀደም ሲል የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በግንባታ ስራ ላይ ካሉ ፋብሪካዎች ባለፉት አምስት ወራት አምስቱ የማሽን ተከላ ስራቸውን አጠናቀው ወደማምረት ተግባር መግባታቸውን አንስተዋል።
ቀሪዎቹ ደግሞ በማሽን ተከላ ስራ ላይ መሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ ፋብሪካዎቹ ፈጥነው የማሽን ተከላ ስራቸውን አጠናቀው ወደማምረት ስራ እንዲገቡ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በማሽን ተከላ ላይ የሚገኙ ሁሉም ፋብሪካዎች ተጠናቀው ወደማምረት ተግባር ሲሸጋገሩ ተኪና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ከማምረት ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩና ለሀገሪቱ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ በማበርከት ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በከተማዋ እስካሁን በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ 268 የተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች በማምረት ስራ ላይ እንደሚገኙ አውስተው፤ ኢንዱስትሪዎቹ በእንጨትና ብረታ ብረት፣ በምግብና ምግብ ነክ፣ በ" ጋርመንት እና ቴክስታይል " የስራ ዘርፎች የተሰማሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከነዚህ ውስጥ 13 ኢንዱስትሪዎች ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርገው የተሰማሩ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከ11 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ከኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያው የተገኘው መረጃ ያሳያል።