ቀጥታ፡

ረቂቅ ደንቡ በእውቀትና በመልካም ስብዕና የታነጸ ትውልድን ለመገንባት አቅም የሚፈጥር ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 5/2018(ኢዜአ)፦በትምህርት ቤቶች አካባቢ አዋኪ ድርጊቶችን ለመከላከል የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብና የተማሪዎች የሥነ ምግባር ረቂቅ መመሪያ በእውቀትና በመልካም ስብዕና የታነጸ ትውልድን ለመገንባት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ገለጹ።

ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ አዋኪ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ ደንብ በማዘጋጀት ተግባር ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ ጀምሯል።

በተመሳሳይ ተማሪዎችን በመልካም ስብዕና ለማነጽ እንደሚያስችል የታመነበት የተማሪዎች የሥነ ምግባር ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጅቷል።

በደንብና መመሪያዎቹ የተለያዩ የሱስ አይነቶች መጠቀምና መሸጥ፣ የኢትዮጵያን ባህል፣ ወግና እሴትን የማይገልፁ የውጭ የሆኑ በዓላትን ማክበር፣ ስልክ ይዞ ወደ ትምህርት ቤት መግባት፣ የመማር ማስተማር ሂደትን የሚያውክ የድምፅ ብክለትን፣የቁማር መጫወቻ ቦታዎችን በትምህርት ቤት አቅራቢያ መክፈት እንደማይፈቀድ ተቀምጧል።

የድል በር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደጀኔ ተስፋዬ በመማር ማስተማር ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደሩ ካሉ ፈተናዎች መካከል በትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚገኙ አዋኪ ድርጊቶች ቀዳሚዎች መሆናቸውን ይናገራሉ።


 

እነዚህ ቦታዎች በአንዳንድ ተማሪዎች ላይ ለሚስተዋሉ የስነ ምግባር ግድፈቶች ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ አዋኪ ድርጊቶችን ለመቆጣጠር ረቂቅ ደንብ እና የተማሪዎች የሥነ ምግባር ረቂቅ መመሪያ ማውጣቱ ተገቢ ነው ይላሉ።

ረቂቅ ደንቡና መመሪያው ተማሪዎች ከትምህርታቸው ወደ ኋላ ከሚያስቀሯቸው አዋኪ ነገሮች በመራቅ በትምህርታቸው እንዲተጉ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክቱም ጠቁመዋል።


 

የአሚጎኒያን ትምህርት ቤት አካዳሚክ ዳይሬክተር ኤሳው አለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የትምህርት ተቋማትን ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ከልዩ ልዩ አዋኪ ድርጊቶች ማላቀቅ ካልተቻለ ሀገርን የሚገነባ ብቁ ዜጋ ማፍራት አዳጋች መሆኑን አንስተዋል።

ከአዋኪ ድርጊቶችና ከስነ ምግባር ጋር በተገናኘ በትምህርት ቤቶች የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ረቂቅ ደንብና መመሪያ መውጣቱ የሚበረታታ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ረቂቅ ደንቡና መመሪያው በተገቢው መልኩ ዳብረው ወደ ተግባር እንዲገቡ የዘርፉ ተዋናዮች የሚጠበቅብንን ሀገራዊ ኃላፊነት መወጣት አለብን ነው ያሉት።

አስተያየት ሰጪዎቹ አይይዘውም ረቂቅ ደንቡና መመሪያው ኢትዮጵያ ያላትን ባህል፣ ወግ እና እሴት በተገቢው መንገድ ለመጠበቅ ፋይዳ እንዳለውም አመላክተዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ፥ መንግስት ተማሪዎች ምቹ በሆኑ የመማር ማስተማር አካባቢዎች እውቀት የሚገበዩበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

እየተከናወኑ ካሉ አበይት ክንውኖች መካከል የትምህርት ስርዓቱን የሚጎዱ አዋኪ ድርጊቶችን መከላከል የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ ነው ብለዋል።

በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ አዋኪ ጉዳዮችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱን በማውሳት።

ይህም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና ተማሪዎች መልካም ስነ ምግባር የተላበሱ እንዲሆኑ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም