የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች መካከል በ10ሩ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። 29 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያስቆጥር ሰባት ግቦችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ30 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባካሄዳቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ስምንቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይቷል። 27 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ የተቆጠረበት አንድ ግብ ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ25 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረ ቡድን ሲሆን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ በሊጉ ዝቅተኛ የግብ መጠን ያስተናገደ ቡድን ነው።
በሊጉ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ክለቦች ጨዋታ በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል።
በሌላኛው መርሃ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከአዳማ ከተማ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ድሬዳዋ ከተማ በ12 ነጥብ ዘጠነኛ፣ አዳማ ከተማ በ14 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።