ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የቀጣናውን ትስስር የሚያጠናክሩ የልማትና የዘላቂ ሰላም ሥራዎችን እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጠናክሩ የልማትና የዘላቂ ሰላም ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

የምስራቅ አፍሪካ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ተጋላጭ መሆኑ ይታወቃል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ  የአፍሪካ ህብረት በ2063 አጀንዳው የያዘውን ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ እንዲሁም የኢኮኖሚ ውህደት የመፍጠር ግብ እንዲሳካ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጣና መሪ ሚና እየተወጣች ነው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዘርፉ ምሁራን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ አበክራ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ ተመራማሪው ከበደ ገርባ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በማልማት ከራሷ አልፋ ጎረቤት ሀገራትን ተጠቃሚ እያደረገች ነው ብለዋል።

በተለይም በቀጣናው የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ወሳኝ መሆኑን አመልክተው፣ ከዚህ አኳያ  ኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል  እያስተሳሰረች መሆኑን ገልጸዋል።


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ የነበራት ሚና ሊረሳ የማይችል ነው ብለዋል።

በቀጣናው ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የወሰደቻቸው እርምጃዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተቸራቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በወዳጅነት መንፈስ ለጋራ ልማትና ዕድገት እየሰራች መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ ጥላሁን ተፈራ (ዶ/ር) ናቸው።


 

በቀጣናዊ ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ማስፈንን ጨምሮ ሁለንተናዊ ትብብርን ለማሳደግና በቀጣናው የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል። 

እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ሰላማዊ ግንኙነት የበለጠ በማሳደግ፣ የጋራ ልማትና ዕድገት ለማረጋገጥ ጥረቷን የበለጠ አጠናክራለች።

የቀጣናው ህዝቦች የጋራ ማንነትና ተመሳሳይ እሴት ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ሃብታቸውን በፍትሃዊነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ሊጠቀሙ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብትና አካባቢ ጥበቃ፣ የቴክኖሎጂ፣ የትምህርትና ስልጠና እንዲሁም የመሰረተ ልማት ግንባታ ስኬቶች ለቀጣናው ሀገራት  ፋይዳቸው የላቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም