ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ ክሪስታል ፓላስ ከማንችስተር ሲቲ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2018 (ኢዜአ):- የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 

ከቀኑ 11 ሰዓት ክሪስታል ፓላስ ከማንችስተር ሲቲ በሰልኸረስት ፓርክ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ክሪስታል ፓላስ በ26 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ማንችስተር ሲቲ በ31 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ31ኛ ጊዜ ነው።  ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 30 ጨዋታዎች ማንችስተር ሲቲ 19 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ክሪስታል ፓላስ አራት ጊዜ ሲያሸንፍ ሰባት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ማንችስተር ሲቲ በ30ዎቹ ጨዋታዎች 63 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ክሪስታል ፓላስ 30 ግቦችን አስቆጥሯል። 

ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በነበራቸው ግንኙነት ማንችስተር ሲቲ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥተዋል። 

በኦስትሪዊው ኦሊቨር ግላስነር የሚመራው ክሪስታል ፓላስ ጥሩ የውድድር ጊዜ በማሳለፍ ይገኛል። 

የፔፕ ጋርዲዮላው ማንችስተር ሲቲ ባለፈው ዓመት ከነበረው መጥፎ የውድድር ዓመት በኋላ ዘንድሮ ጠንካራ ግስጋሴ እያደረገ ነው።

በፕሪሚየር ሊጉ ከምርጥ አራቱ ሁለቱ የሆኑት ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ማንችስተር ሲቲ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጋል።

የ39 ዓመቱ ዳረን ኢንግላንድ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል። 

በሌሎች መርሃ ግብሮች ሰንደርላንድ ከኒውካስትል ዩናይትድ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት ከቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ዌስትሃም ዩናይትድ ከአስቶንቪላ በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

ብሬንትፎርድ ከሊድስ ዩናይትድ ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም