ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ለቀጣይ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ስኬት መሰረት የጣሉበት ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነው አኩሪ ታሪክ የሰሩበትና ለቀጣይ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ስኬት መሰረት የጣሉበት ነው ሲሉ  የጉምሩክ ኮሚሽን አመራር አባላት ገለጹ፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን አመራር አባላት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉወርቅ ደረሰ እንዳሉት፤ ግድቡ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ኮሚሽኑ ከመጀመሪያው ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል።


 

ለግድቡ የሚውሉ የተለያዩ ግብዓቶች በተሳለጠ መልኩ ተደራሽ እንዲሆን ኮሚሽኑ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራቱን ለአብነት አንስተዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን የህግ ተገዥነት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አዝዘው ጫኔ በበኩላቸው፤ ለህዳሴ ግድብ ይውሉ ለነበሩ ግብዓቶች ቅድሚያ ተሰጥቶ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ጠቁመው፤ ግድቡ ጀምሮ መጨረስ በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑን አስታውቀዋል። 


 

ምክትል ኮሚሽነሩ፤ግድቡ የኢትዮጵያን ታላቅነት ለዓለም ያስመሰከረ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን አብሳሪ መሆኑን ገልጸው፤  ኢትዮጵያውያን በትብብር እውን ያደረጉት ትውልድ ተሻጋሪ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በኮሚሽኑ የባህርዳር ቅርንጫፍ ኃላፊ አለነህ ማሃሪ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ምንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል በህዳሴ ግድብ ማረጋገጥ የቻልንበት ነው ብለዋል።  

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ ግድቡ የሚያመነጨው ኃይል ከኢትዮጵያም አልፎ  ለጎረቤት አገራትም የኃይል ፋላጎት በማሟላት ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።  


 

ለግድቡ ስኬት የሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ፕሮጀክቱ ለቀጣይ ስራዎች ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል። 

ኮሚሽኑ የግድቡ ግንባታ ከግብ እንዲደርስ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም