ቀጥታ፡

የባሕርዳር ‎የኮሪደር ልማት ከጣና ሐይቅ ዳርቻ ጋር ተሳስሮ መልማቱ የከተማዋ ውበት ይበልጥ እንዲገለጥ አስችሏል

ባሕርዳር /ደብረብርሀን ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ ‎የባሕርዳር   የኮሪደር ልማት ከጣና ሐይቅ ዳርቻ ጋር ተሳስሮ እንዲለማ መደረጉ የከተማዋ ውበት ይበልጥ እንዲገለጥ  ማስቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ፣ ‎የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋን ጨምሮ  ሌሎችም ከፍተኛ  የመንግስት የስራ ሃላፊዎች  የባሕርዳርን  የልማት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።

ከጎበኟቸው ልማቶች መካከል   የኮሪደር ልማት፣ የአረንጓዴ መናፈሻ፣ የመንገድ፣  መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትና የባሕርዳር አለም አቀፍ ስታዲየም ይገኙበታል።


 

‎‎ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤  ደረጃቸውን ጠብቀው እየተገነቡ የሚገኙ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ስራዎች የከተማዋን ገፅታ በእጅጉ እየቀየሩ ይገኛል።

‎‎የኮሪደር ልማቱ ከጣና ኃይቅ ዳርቻ ጋር ተሳስሮ  መልማቱ የከተማዋ ውበት ይበልጥ እንዲገለጥ በማድረጉ የቱሪስቶች  መዳረሻ ማዕከል እንድትሆን ማድረጉን  ተናግረዋል።


 

የከተማዋ የልማት ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መደረጉ  የሚበረታቱ  ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ‎በቀጣይም የመኖሪያ ቤት ልማት እንዲስፋፋ፣ የአገልግሎት አስጣጥ እንዲሻሻልና ሌሎች  ሕዝቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም ሀሳብ አንስተዋል።

‎‎‎የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፤  ባሕርዳር ለሌሎች ከተሞች ምሳሌ ልትሆን በሚያስችላት አስደማሚ የለውጥ ጎዳና ላይ የምትገኝ ከተማ መሆኗን ገልጸዋል። 


 

‎ከተማዋ በተፈጥሮ የተቸራትን ፀጋ  ይበልጥ በኮሪደር ልማት አጉልቶ በማውጣት የተደረገው ጥረት ከተማዋ ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል። 

‎‎እየተከናወኑ የሚገኙ የኮርደር ልማት ስራዎች   ለቱሪዝም መነቃቃት እንዲፈጠርና ገፅታዋ እንዲቀየር ያስቻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

‎በተመሳሳይ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች  በደብረብርሀን ከተማ  የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን  እንዲሁም የኮሪደር ልማትን ጎብኝተዋል።


 

ከጎብኚ አመራሮች መካከል በአሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር)  ፤  በደብረብርሀን ከተማ  እየተከናወኑ ያሉት  የኢንቨስትመንት ስራዎች   የሚበረታቱ   መሆናቸውን  ተናግረዋል።


 

ኢንዱስትሪዎች  ከአካባቢው አርሶ አደሮች  ግብአትነት  በመጠቀም የገበያ ትስስር መፍጠራቸውን  አንስተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች  ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው፤  የደብረብርሃን  የኢንዱስትሪ  እንቅስቃሴዎች  ከተማዋ ለኢንቨሰትመንት ምቹ መሆኗን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።


 

በተለይ ተኪና ለውጭ የሚላክ  ምርት በማምረት ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች  አበረታች እንቅስቃሴ ላይ እንደሆኑ ከጉብኝቱ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

የደብረብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ፤ በአካባቢው ሰላምን ከማፅናት ጎን ለጎን  የልማትና  የኢንቨስትመንት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም