በፀጥታና ደህንነት ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጉባዔዎችን በስኬት ለማስተናገድ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በፀጥታና ደህንነት ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጉባዔዎችን በስኬት ለማስተናገድ አስችሏል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦በፀጥታና ደህንነት ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ዓለምአቀፍ እና አህጉራዊ ጉባዔዎች በስኬት እንዲስተናገዱ ማስቻሉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
የፀጥታና ደህንነት ተቋማት 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ- 32) በስኬት እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑም ተገልጿል።
"ጠንካራ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት የእውቅናና ምስጋና መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው።
መርኃ ግብሩ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የተዘጋጁ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ጉባኤዎችና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከበሩ ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት በስኬት መጠናቀቃቸውን አስመልክቶ እንደሆነ ተገልጿል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ ጉባዔዎችን እንዲሁም ታላላቅ ሀገራዊ በዓላትን በታላቅ ስኬትና ሰላማዊ ሁኔታ ማስተናገድ ችላለች።
እነዚህ ክስተቶች የሀገሪቷን የዲፕሎማሲ አቅም፣ የደህንነት ጥበቃ ብቃት እና ህዝባዊ ትብብር ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።
በጸጥታና ደህንነት ተቋማት መካከል የነበረው ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ ለስኬታማነቱ አይተኬ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።
በጉባዔዎቹ የእንግዶችን ደህንነት ከማረጋገጥ ባሻገር፣ በመዲናዋ የተረጋጋ ሁኔታን በመፍጠር ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ያለምንም እንቅፋት እንዲካሄዱ መደረጉን አመልክተዋል።
ለዚህም በፀጥታና ደህንነት ተቋማት የተከናወኑት የሪፎርም ሥራዎች ዓለምአቀፍና አህጉራዊ ጉባዔዎችን በስኬት ለማስተናገድ አስችሏል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባዔን (ኮፕ- 32) እንድታስተናግድ መመረጧ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን ገልፀው፤ ይህ ጉባዔ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ከወዲሁ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም ለዓለም እና ለአፍሪካ ኢንተር ፖል ጉባዔም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።