ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአፋር ክልል ህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነቱ በተግባር እውን ሆኗል - የሰመራ ሎጊያ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአፋር ክልል ህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነቱ በተግባር እውን ሆኗል - የሰመራ ሎጊያ ነዋሪዎች
ሰመራ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአፋር ክልል ህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነቱ በተግባር እውን መሆኑን የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
"የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው ዕለት በሰመራ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
የመድረኩ ተሳታፊ የሰመራ ሎጊያ ነዋሪዎች ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአፋር ክልል ህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነቱ በተግባር እውን ሆኗል ብለዋል።
በክልሉ የመስኖ ልማትን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ስራዎችም በስፋት እየተከናወኑ በመሆኑ ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የሚደረገው ጥረት እየተሳካ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ መሐመድ አብዱልቃድር በአፋር ክልል የተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ የልማት ስራዎች ለሀገርም ጭምር የሚጠቅሙ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት በነበረው የመንግስት አስተዳደር የክልሉ ህዝብ የፖለቲካ ተሳትፎና የልማት ተጠቃሚነት ፍትሃዊነት የጎደለው እንደነበር አንስተው በለውጡ እኩልነትና ፍትሃዊነት በተግባር ተረጋግጧል ብለዋል።
በክልሉ ወጣቱን ማዕከል ያደረጉ የልማትና የስራ ዕድሎች እየተመቻቹ መሆኑን ያነሳው ወጣት አሊ ሰላል፤ በዚህ ረገድ ጅምሮች ቢሆኑም በቀጣይ ብዙ መሰራት እንዳለበት አንስቷል።
በተለይም ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ወንጀልን ለመከላከል ወጣቶችን በጥሩ ስነ ምግባር መቅረጽና በቂ የስራ እድል መፍጠር ይገባል ብሏል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)፤ በሁሉም አካባቢዎች የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የሀገርን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ መንግስት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፋር ክልል የተከናወኑ እና በመከመናወን ላይ ያሉ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎች ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆናቸውን አንስተው የህዝቡ ጥረትና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ከግብርና በተጨማሪ በኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና የዲጂታል ልማት ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ የጋራ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።
የለውጡ መንግስት አሳታፊና ህብረ ብሔራዊ አንድነት የተረጋገጠባት ጠንካራ ሀገር የመገንባት ዓላማ ሰንቆ እየሰራ ስለመሆኑ አንስተው በዚህም እመርታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የፍትህ ሚኒስትሯ ሐና አርዓያስላሴ በበኩላቸው እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ማእከል ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ገና ያልተነካ እምቅ የመልማት አቅም ያለ መሆኑን አንስተው በተለይ ወጣቶች ያለውን ፀጋ በመጠቀም በሀገራቸው ሰርተው ለመለወጥ በትጋትና በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው ብለዋል።