በኢትዮጵያ ዋንጫ ኢትዮጵያ መድን እና መቻል ለሩብ ፍጻሜ አለፉ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዋንጫ ኢትዮጵያ መድን እና መቻል ለሩብ ፍጻሜ አለፉ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዋንጫ ሶስተኛ ዙር የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነዋል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ቢሾፍቱ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል።
አማኑኤል ኤርቦ እና ዩጋንዳዊው አለን ካይዋ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ መቻል ድሬዳዋ ከተማን በመለያ ምት አሸንፏል።
ጨዋታው በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ አቻ አጠናቋል።
ዮዳሄ ዳዊት ለመቻል እና ጃፋር ሙደሲር ለድሬዳዋ ከተማ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። መቻል በመለያ ምት 5 ለ 4 ማሸነፍ ችሏል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ መድን እና መቻል ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል።
ዛሬ በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች ነጌሌ አርሲ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማን፣ ቦዲቲ ከተማ ባህር ዳር ከተማን በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ አልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዋንጫ ሶስተኛ ዙር ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ ይደረጋሉ።