በከተማው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
ወላይታ ሶዶ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ በወላይታ ሶዶ ከተማ ህዝቡ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የከተማው ነዋሪዎች አመለከቱ።
ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት "የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች'' በሚል መሪ ሀሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ታደሰ ሌራ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም ስናነሳቸው የነበሩ የልማት ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ምላሸ እያገኙ ነው ብለዋል።
በተለይም በሰላምና ጸጥታ ዘርፍ የተሰራው ስራ የወላይታ ሶዶ ከተማን እንቅስቃሴ የተረጋጋና ሰላማዊ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል በከተማው የስራ አጥነት፣ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የመንገድ ግንባታዎች፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት፣ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት አለመዘመን ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶች እንዲጠናከሩ ጠይቀዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አልማዝ አንጁሉ እንደገለጹት በከተማው የህዝቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበሩ የመንገድ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ እና ሌሎችም ልማቶች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የከተማውን ውበትና እድገት የሚያፋጥን የኮሪደር ልማት ስራም እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
ይሁንና የተጀመሩ የልማት ስራዎች ላይ መጓተት እየተስተዋለ በመሆኑ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በከተማው የህዝብ ጥያቄን መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ ላቴኖ ላቁ ናቸው።
ከተማው በርካታ ስፖርተኞች የሚወጡበት በመሆኑ ለዘመናዊ ስታዲየም ግንባታም ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ችግር ለመፍታት የተጀመረው ስራ ከዳር እንዲደርስ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው የወላይታ ሶዶ ከተማ በፈጣን ዕድገት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው ከተማውን ለመለወጥ የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
በከተማው የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን እንደሚገባም አመልክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከፍያለዉ ተፈራ ያለንን የሰው ኃይል፣ ለም መሬት፣ ውሃ እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን በመጠቀም ለስኬታማነቱ መረባረብ ይገባል ብለዋል።
የሀገርን ከፍታ የሚያረጋግጡ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ተፈሪ አባተ በበኩላቸው በክልሉ የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ወጣቶች የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ማግኘት የሚያስችሏቸው ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።
ህዝቡ በተደጋጋሚ ሲያነሳቸው የነበሩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው የስቴዲየም ግንባታ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም እንዳሉት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ስራዎች በጥራትና በፍጥነት እየተከናወኑ ነው።
ነዋሪዎችን ጭምር በማሳተፍ ከተማውን ንጹህ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተው ህዝቡ ለልማት ስራዎች ስኬታማነት የጀመረውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር አስገንዝበዋል።