የህዝብን የልማት ተጠቃሚነትና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብን የልማት ተጠቃሚነትና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 4/2018 (ኢዜአ) ፡-የህዝብን የልማት ተጠቃሚነትና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
“የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግስት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ሀሳብ በሀዋሳ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የውይይት መድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ በብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ መለስ ዓለሙ እና ሌሎችም የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች በለውጡ ዓመታት ህብረብሔራዊ አንድነትን በማስጠበቅ ለህዝብ የልማት ተጠቃሚነት፣ ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ መንግስት ያደረገው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ እና ሀጂ ኡመር ሁሴን፤ በለውጡ ዓመታት የተከናወኑ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።
በሲዳማ ክልል ያሉ እምቅ ሃብቶችን በማልማት በሁሉም መስኮች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶችም ትልቅ ተስፋ የተሰነቀባቸው መሆኑን ነው የተናገሩት።
በከተሞች የኮሪደር ልማት ስራን ጨምሮ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችን በማልማትና የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የተከናወኑ ተግባራትም የሚደነቁ መሆናቸውን አንስተዋል።
ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ ጋሻው ምትኬ (ዶ/ር)፤ በለውጡ ዓመታት በፕሮጀክቶች ክንውን፣ የግብርና ልማትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ተጨባጭ ውጤት መጥቷል ብለዋል።
በመልካም አስተዳደርና በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ጥሩ ጅምሮች ቢኖሩም በቀጣይ ብዙ የተቀናጀ ሥራ ይጠይቃል ሲሉ አጽእኖት ሰጥተዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጥራቱ በየነ፤ የሀዋሳ ከተማን እምቅ ሃብቶች በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት መዳረሻ የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል፡፡
የሐይቁን ዳርቻ አሁን ላይ ለነዋሪዎችና ለቱሪስቶች ምቹ ማሪፊያ በሚሆን መልኩ ደረጃ በደረጃ የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።
የሀዋሳ ስታዲየም ግንባታን የማጠናቀቅ፣ በሀዋሳ ጉዱማሌ እየተገነባ ያለውን የባህል ማዕከል፣ የአዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ፣ የታቦር ተራራ ልማትና ሌሎችም ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለስ ዓለሙ፤ መንግስት ላከናወናቸው ስራዎች ዕውቅና በመስጠት ሊሟሉ የሚገቡ ጉዳዮች መነሳታቸው በቀጣይ ለሚሰሩ የልማት ሥራዎች አስቻይ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራዎች የመንግስት ትኩረቶች ሆነው ይቀጥላሉ ሲሉ ገልጸዋል።
በሀዋሳ ከተማ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አንስተው ለስኬት እንዲበቁ የመንግስት ጥረት እንዳለ ሆኖ ህዝቡም ትብብርና እገዛውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።