ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ቅርሶችና የመስህብ መዳረሻዎች እንዲለሙና እንዲተዋወቁ አቅም ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ቅርሶችና የመስህብ መዳረሻዎች እንዲለሙና እንዲተዋወቁ አቅም ፈጥሯል
ዲላ ፤ ታህሳስ 4/2018 (ኢዜአ) ፡- ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ቅርሶችና የመስህብ መዳረሻዎች እንዲለሙና እንዲተዋወቁ አቅም መፍጠሩን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ገለጸ።
የጌዴኦ ባሕላዊ መልከዓ ምድር አለም አቀፍ ቅርስ ዘለቄታዊ ጥበቃና እንክብካቤ ዙሪያ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሕይወት ኃይሉ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ያላትን ቅርሶች በመጠበቅ፣ የቱሪስት መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
በተለይም የቅርሶችን ደሕንነት ለማረጋገጥ የማሕበረሰብ አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
የጌዴኦ ባሕላዊ መልከዓ ምድርም በአግባቡ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሀገር በቀል እውቀትና ባሕላዊ እሴቶች ሃብት የበለጸገ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይኒቱ መልኩ ናቸው።
ለዚህም የጌዴኦ ባሕላዊ መልከዓ ምድር ጥሩ ማሳያ መሆኑን አንስተው፤ ባሕላዊ እሴቶቹ ለሰላም ግንባታና ለሕዝብ ትስስር ካላቸው ፋይዳ ባለፈ የቱሪዝም ሃብቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባሕላዊ ቅርሶችን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲሸጋገሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) ፤ የጌዴኦ ባሕላዊ መልከዓ ምድር ጥምር ግብርና፣ የትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስ፣ ጥብቅ ደኖችንና የድንጋይ ላይ ጽሑፎችን ያካተተ ብዝሃ መስሕብ ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።
መልከዓ ምድሩን ከባሕላዊ ስርዓት ጋር በማስተሳሰር በዘላቂነት እንዲጠበቅ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይ የመስህብ መዳረሻዎችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን ከማሳደግ ባለፈ ጥናትን መሰረት ያደረገ ዘላቂ የመሬት አጠቃቀም ተግባራዊ መደረጉንም አንስተዋል።
በመድረኩ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች፣ የዘርፉ ምሁራን፣ የባሕል አባቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።