የአማራ ክልልን ሰላም ለማጽናትና የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደግፋለን - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልልን ሰላም ለማጽናትና የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደግፋለን
ባሕር ዳር ፤ ታህሳስ 4//2018 (ኢዜአ)፡- የአማራ ክልልን ሰላም ለማጽናትና የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደግፋለን ሲሉ የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
"የጉባ ብስራቶች፤ የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።
በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የክልሉን ሰላም ለማጽናትና የህዝቡን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የመንግስት ያላሰለሰ ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ የመንግስት ጥረት ውስጥ የጸጥታ አካላት፣ በየደረጃው ያለው አመራርና የህዝቡም ተሳትፎ ትልቅ መሆኑን አንስተው የከተማዋ ነዋሪዎችም ይህንኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሙሉ ምትኩ፤ የለውጡ መንግስት በሁሉም አካባቢዎች ለትውልድ የሚተርፉ የልማት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በማጠናቀቅ ጥቅም ላይ እያዋለ ይገኛል ብለዋል።
በባህር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት በተጨባጭ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታቸው እየታየ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በመሆኑም የአማራ ክልልን ሰላም ለማጽናትና የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ በመሆኑ ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉም ተናግረዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ወርቁ አላምረው፤ የባህር ዳርን ውበት ከጣና ሃይቅ ጋር በማስተሳሰር የጎርጎራ ግዙፍ ፕሮጀክትና ሌሎችም የልማት ስራዎችን ማድነቅ የግድ ይላል ብለዋል።
እንደ ሀገር በርካታ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ክንውን እና የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ለማሳካት የሚደረጉ ጥረቶችም የጋራ ተስፋ የሰነቅንባቸው ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ የዝቡጥላ ካሳ፤ በተለያዩ ችግሮች ውስጥም ሆኖ መንግስት እያከናወናቸው ያሉ የልማት ስራዎች ይበል የሚያሰኙ መሆናቸውን አንስተው በቀጣይ የኑሮ ውድነትና ብልሹ አሰራርን የመከላከል ጥረት ትኩረት ይሻል ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባልና የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፤ በሁሉም መስክ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማጠናከር የህዝብን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች በማዳመጥ ተግባራዊ ምላሽ ከመስጠት በተጨማሪ ለችግሮች መፍትሄ የመፈለግ ስራም የመንግስት ትኩረት መሆኑን አንስተው የመድረኩም አላማ ይሄው መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ ሀይሎች ዐይን ማረፊያ በመሆኗ ለማደግና የሕዝቦቿን ኑሮ ለመለወጥ በምታደርገው ጥረት ታሪካዊ ጠላቶች በባንዳዎች በኩል ለማሰናከል እየጣሩ መሆኑን አንስተው የተጀመረውን የለውጥና እድገት ግስጋሴ ሊያስቆማት የሚችል ሃይል የለም ብለዋል።
ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ የሚነሳው ጥያቄ ተገቢ መሆኑን አንስተው መንግስት ነባራዊ ሁኔታውን ታሳቢ በማድረግ ችግሩን ለማቃለል ጥረቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ግብርናን በማዘመንና ምርታማነትን በማሳደግ ከውጭ ይገባ የነበረን ስንዴ በራስ አቅም በማምረት ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶቿ እንደተመኙት ወደ ኋላ የቀረች ሳትሆን በርካታ ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎችን እያከናወነች የቀጠለች መሆኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልልን ሰላም ለማጽናትና የህዝቡን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግስት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው፤ የከተማዋን ሰላም የማጽናትና የልማት ስራዎችን በጥራት የማከናወኑ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በከተማው ገበያን ለማረጋጋት አምራቹና ሸማቱ ቀጥታ የሚገናኙበት የገበያ ማዕከል እየተመቻቸ መሆኑን አንስተው፤ ምርት ያለአግባብ በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም አመልክተዋል።
በመድረኩ ላይ የሀይማኖት አባቶች፣ ነጋዴዎች፣ ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።