በክልሉ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ውጤት እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ውጤት እያመጣ ነው
ወልቂጤ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ውጤት እያመጣ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
"ወባን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል" በሚል መሪ ሀሳብ በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ በአዶሼና አቶርቸ ቀበሌ የወባ ሳምንት ተከብሯል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተከናወነው የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ውጤት እያመጣ ነው፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን በማጠናከር የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ፣ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የአልጋ አጎበር ስርጭትና የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ህይወት ሰለሞን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት የወባ በሽታን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ስራውን አጠናክሮ በማስቀጠል የወባ በሽታን ለማጥፋት ባለድርሻ አካላትን ላሳተፈ ቅንጀታዊ ሥራ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
እንደ ህይወት (ዶ/ር) ገለጻ፤ ባለፈው ዓመት በ222 ወረዳዎች የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት የተካሄደ ሲሆን 5 ነጥብ 9 ሚሊዮን አጎበርም ለህብረተሰቡ ተሰራጭቷል።
በዚህ ዓመትም ህብረተሰቡን በማሳተፍ ውሃ ያቆሩ ስፍራዎችን የማዳፈን፣ የአልጋ አጎበሮችን የማሰራጨትና የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አክለዋል።
በዞኑ 11 ወረዳዎች የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ትኩረት ተድርጎ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ ናቸው።
የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከልና የግንዛቤ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
በቸሃ ወረዳ የአዶሼና አቶርቸ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እድሉ ገብሬ፤ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በሚሰጧቸው ሙያዊ ምክር ታግዘው የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የማጽዳትና ውሀ የሚያቁሩ ስፍራዎችን የማዳፈን ሥራ ማከናወናቸውን ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ በወባ መራቢያ መንገዶች ላይ ግንዛቤ ማግኘቱ አካባቢውን በጋራ ከማጽዳት ባለፈ የአልጋ አጎበርን በመጠቀም ራሱን ከወባ በሽታ ለመጠበቅ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር የተከበረው የወባ ሳምንት እንደ ሃገር ለ7ኛ ጊዜ እንደ ክልል ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።