ቀጥታ፡

የተጀመሩ የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ የዘላቂ ሰላም ግንባታ ጉዳይ የጋራ አጀንዳችን ሆኖ ይቀጥላል

ደሴ ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የተጀመሩ የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ የዘላቂ ሰላም ግንባታ ጉዳይ የጋራ አጀንዳችን ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

"የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግስት ቱሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በደሴ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል።


 

የመድረኩ ተሳታፊዎች ሸሕ ኢሳ ፣ወይዘሮ ብርቱካን ታደሰ እና አቶ እንድሪስ መሀመድ በሪሁን እንደገለፁት፣ መንግስት ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ሰላምን በመጠበቅ ልማትን ለማስፋፋት የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው።

በከተማው የመንገድ አውታሮችን በማስፋት እና የስራ እድል መፍጠሪያ ሼዶች በመገንባት እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች የሚበረታቱ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በተለይ የአስፋልት መንገድ፣ መሶብ አንድ ማዕከል፣ የሕዝብ መድሃኒት ቤቶች፣ የጤና እና የትምሕርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

በከተማው በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ፣ በመብራት ሃይል ማነስና መቆራረጥ፣ በመሬት መንሸራተትና በክረምት ጎርፍ መከላከል ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ ጠይቀዋል።

ቀደም ሲል በመንግስት ቃል የተገቡና የተጀመሩ የደሴ-ኮምቦልቻ አቋራጭ መንገድ፣ ወሎ ቴሪሸሪ ኬር ሆስፒታል ግንባታ፣ አዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ የባቡር መንገድ ግንባታ፣ የመኖሪያ ቤት ችግር፣ ስርዓት አልበኝነት፣የኑሮ ውድነትና ስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።


 

የሰላም ጥሪውን በማይቀበሉ ሽፍቶችና ተላላኪዎች ላይም መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ አመልክተው፤ መንግስት በሰው ተኮር ፕሮጀክቶች የድሆችን እንባ እያበሰ በመሆኑ እኛም ሁለተናዊ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ሆኖም በለውጡ መንግስት ያገኘነውን ልማት ለማውደም፣ የተጀመሩን ልማቶች ለማደናቀፍ የሚታትሩ የግል ጥቅመኞችን ማስተካከል ይገባል፣ እኛም ከመንግስት ጎን ተሰልፈን ልማታችንን እናስቀጥላለን ብለዋል።

ተተኪ አመራር መፍጠር፣ ወጣቱን ማብቃት፣ ለወጣቱ መዝናኛ ማመቻቸትና በከተማው ደረጃውን የጠበቀ ስታዲዮም መገንባትና የጋራ ትርክትን ማጎልበት እንደሚገባም አንስተዋል።

ነዋሪዎቹ ፤ ተጀመሩ የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ የዘላቂ ሰላም ግንባታ ጉዳይ የጋራ አጀንዳችን ሆኖ መቀጠል አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡን በማስተባበር ሰላሙን ከማስጠበቅ ባለፈ በለውጡ መንግስት ሰፋፊ የልማት ስራዎችን ማከናወን ተችሏል ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ናቸው።


 

በከተማው የተከናወኑ አስፋልት መንገድ፣ የኮሪደር ልማት፣ መሶብ አንድ ማዕከል፣ ሌማት ቱርፋትና ሌሎችም በለውጡ መንግስት የተከናወኑና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ያስቸሉ የልማት ተግባራት ናቸው ብለዋል።

ሕብረተሰቡ ላነሳቸው ጥያቄዎችም ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት ተገቢው ክትትልና ጥረት እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍስሃ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ሕዝቡ የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል።


 

ግብርናውን በማዘመን፣ ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ ገበያን በማረጋጋትና በሌሎችም ሪፎርሞች ተጨባጭ ውጤት በማስመዝገብ ለሕዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት ተችሏል ብለዋል።

አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ከሰላም ጥሪው በተጓዳኝ ሕግ የማስከበር ስራው ይቀጥላል ብለዋል።

የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን የበለጠ በማጠናከር የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ደግሞ በመድረኩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ ናቸው።


 

በሀገሪቱ ሕግ በማስከበር ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ሂደትም ሁሉም በመደገፍ የባዳና የባንዳን ተልዕኮ ለማክሸፍ መረባረብ ይገባናል ብለዋል።

የወሎን የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የመቻቻልና የመረዳዳት ባሕል ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በደሴ ከተማ የተመለከትነው ልማትና ያደረግነው ውይይት ለብልጽግና ጉዟችን ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሽዊት ሻንካ በበኩላቸው፣ በሃገሪቱ በኢኮኖሚው፣ በማሕበራዊና በፖለቲካው ዘርፍ የተመዘገቡ ድሎች የኢትዮጵያን ማንሰራራት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።


 

በተለይ በስንዴ ልማት፣ ኮሪደር ልማት፣ ከተማ ልማት፣ በሌማት ቱርፋት፣ በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትና በሌሎችም ዲጂታል ቴክኖሎጂ አሰራሮች የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በውይይቱ የተነሱ ሐሳቦችንም የእቅድ አካል በማድረግ የሕብረተሰቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በመድረኩም የፌዴራልና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም