ጤናማ እና አምራች ዜጋን በማፍራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ልማድ ማድረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ጤናማ እና አምራች ዜጋን በማፍራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ልማድ ማድረግ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ ጤናማ እና አምራች የሰው ሀይልን በማፍራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ልማድ ማድረግ እንደሚገባ ተመላከተ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ያስገነባውን የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ አስመርቋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ስፖርት የሰዎችን ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር አብሮ የመስራት ባህልን የሚያጎለብት ነው።
ኢንዱስትሪዎች የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት የሚሰሯቸውን ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ አምራች የሰው ሀይል የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል።
በመሆኑም የሰው ሀይላቸውን በአግባቡ ለመጠቀም፣ ውጤታማ ለማድረግና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች ዜጋ መገንባት ግድ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የተገነባው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራም የኢኮኖሚ ዞኑ ሰራተኞች እና የአካባቢው ማህበረሰብ የሚገለገልበት መሆኑን አስታውቀዋል።
የቂሊንጦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዋና ሥራ አስኪያጅ ቶሎሳ በዳዳ በበኩላቸው፤ የስፖርት ማዘወትሪያ ስፍራዎቹ ሰራተኞቹ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራው የእግር ኳስና የቅርጫት ኳስ ጨምሮ ሌሎች የስፖርት ዓይነቶችን ማከናወን የሚያስችሉ ስፍራዎችን ማካተታቸውን ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አለምነህ ስዩም እንደ ሀገር ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።