ቀጥታ፡

በሕዝብና በመንግስት ጠንካራ ቅንጅት የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስቀጠል የበኩላችንን እንወጣለን

ጎንደር፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ በሕዝብና በመንግስት ጠንካራ ቅንጅት የተመዘገቡ ወጤቶችን በማስቀጠል ለጉባ ብስራት የልማት ግቦች መሳካት የሚጠበቅባቸውን ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የጎንደር ከተማ የህዝባዊ መድረክ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

በጎንደር ከተማ የተገነቡ የቅርስ ጥበቃና የመሠረት ልማት ስራዎችን በማድነቅ የንጹህ መጠጥ ውሃና የኃይል አቅርቦት፣ የዘላቂ ሰላም ግንባታና የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የተሟላ የመሠረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል አረጋግጠዋል።

የጎንደር ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች "የጉባ ብስራቶች፥ የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ ከፌዴራል፣ ክልልና ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ጋር መክረዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በመድረክ መልዕክታቸው፥ ኢትዮጵያ ከህዝቦቿ እሴትና ጸጋ የሚመነጭ የልማት አቅም እየፈጠረች ነው ብለዋል።


 

የጥበብ ማማና እንግዳ አክባሪ የሆነችው ጎንደር ታሪኳን የሚመጥን የልማት ሥራ ላይ መሆኗን ገልጸዋል።

በቀጣይም በኢትዮጵያ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት በአራቱም ማዕዘናት በሁሉም መስክ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) ለመድረኩ መነሻ በጎንደር ከተማ በአማራ ክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችና የቀጣይ የህዝብና መንግስት የልማት አቅጣጫዎችን አቅርበዋል።

በዚህም ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የጎንደር ህዝብ የኢትዮጵያ አንድነትና ሕብረ ብሔራዊ ትሥሥር፣ ዘላቂ ሰላምና ሙስና፣ የመልካም አስተዳደርና ጉልህ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ሲያነሳ እንደነበር አስታውሰዋል።


 

በዚህም በጎንደር ከተማም የኢትዮጵያን የመካከለኛ ዘመን የታሪክ መነሻነት በሚመጥን መልኩ ትናንትን ከዛሬ በማስተሳሰር ዛሬን ከነገ የሚያጋምድ ልማት መሰራቱን ተናግረዋል።

የክልሉና የፌዴራል መንግስት በዘላቂ ሰላም ግንባታ መርህ የጽንፈኛ ኃይሎችን የጥፋት ተልዕኮ በማክሸፍ አስተማማኝ የሕግ የበላይነት የሚያረጋግጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የመደመር መንግሥት ለብዝኅ ኢኮኖሚ የሰጠው ትኩረት በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና ማዕድን መስክ በክልልና ሀገር አቀፍ ደረጃ እመርታዊ ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ ፈጠራን ከፍጥነት በማሰናሰል በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ መስክ የውስጥና የውጭ አሻጥርና ሴራ ያልገደበው ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት የሚያደርጉ አኩሪ ድሎች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች፥ በጎንደር ከተማ የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስት ዕድሳት፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ የኮሪደርና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ታሪክና ዘመናዊነትን ያሰናሰሉ ናቸው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጎንደር ከተማን ታሪክ በሚመጥን መልኩ ስኬታማ የልማት ስራዎች እንዲሰሩ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የመንግስትን የሰላም አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች የክልሉንና የሀገርን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የኃይል አቅርቦት፣ ዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን የማረጋጋትና ሌሎች ምላሽ የሚሹ ጉዳዮችን ጠይቀዋል።

በሀገራዊ ምክክር መፍትሔ የሚሹ የጋራ ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ለጉባ ብስራት የልማት ግቦች ስኬት በትጋት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።


 

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በመድረኩ ለተነሱ ጉዳዮች በሰጡት ምላሽ፥ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በገዛ ልጆቻችን አማካኝነት የጥፋት ተልዕኳቸው ተሸካሚ እያደረጉ ነው ብለዋል።

በዚህም የትህትና መገለጫ የሆነው የጎንደር ህዝብ በተሳሳተ መንገድ የቆሙ ልጆችን በመምከር የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ የማድረግ ኃላፊነት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

በቀጣይም የጎንደር ከተማንና የኢትዮጵያን የተሟላ የመሠረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)፥ በመድረኩ በተነሱ አስተያየትና ጥያቄዎች ለተሰሩት ዕውቅና ቀሪ ስራዎችን በማመላከት የቀረቡ ሃሳቦች የጎንደርን ህዝብ ሚዛናዊነት ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።

በጎንደር የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስት ዕድሳትና የኮሪደር ልማት የተሰጠው ዕውቅና ለበለጠ የልማት ትጋት ጉልበትና ብርታት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።


 

በቀጣይም መንግሥት በህዝብ ተሳትፎ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ የልማት ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፥ የከተማዋን የልማት ትንሳኤ የሚያበስሩ ስኬቶች የጎንደር ከተማ ህዝብና መንግስት የትብብር ውጤት ናቸው ብለዋል።

በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎች ያነሷቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም