በአካባቢው እምቅ ሀብቶች ለምተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለተጀመሩ ተግባራት ስኬት የበኩላችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
በአካባቢው እምቅ ሀብቶች ለምተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለተጀመሩ ተግባራት ስኬት የበኩላችንን እንወጣለን
አርባምንጭ ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ):-የአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢው እምቅ ሃብቶች ለምተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተጀመሩ ጥረቶችን እናግዛለን ሲሉ የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ።
"የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ በአርባምንጭ ከተማ ህዝባዊ ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
ከአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎቸ መካከል አቶ ለማ ፖሎ በሰጡት አስተያየት፤ የመደመር መንግስት በአርባምንጭ ከተማ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት በማከናወን ከተማውን ከጎርፍ አደጋ ስጋት በመታደግ ተጠቃሚ አድርጎናል ብለዋል።
በተጨማሪም ትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማትን በመገንባት እንዲሁም የመንግስት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በማድረግ የህዝቡን ማህበራዊ ልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል በአትክልትና ፍራፍሬ እምቅ አቅም ላለው አርባምንጭ ከተማና አከባቢው የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንዲቋቋም ጠይቀዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ በለጠ በቀለ በበኩላቸው፤ መንግስት በሀገሪቱ ህዝብን የሰላምና የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል ።
በአካባቢውም የተለያዩ ልማቶች መከናወናቸውን ጠቁመው የገበታ ለትውልድ ኮንፈረንስ ሪዞርት እንዲሁም የአርባምንጭ ስታዲየም ግንባታ የመደመር መንግስት ትሩፋቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የለውጡ መንግስት የሴቶችን እኩልነት ከማረጋገጥ በላይ በውሳኔ ሰጪነትና በስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ አድርጓል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሰላምነሽ ሠመረ ናቸው።
በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንድንላቀቅ አስችሎናል ሲሉም አክለዋል ።
ነዋሪዎቹ መንግስት በአርባምንጭ ከተማና አካባቢው እምቅ ሃብቶች ለምተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለጀመራቸው ጥረቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጥዋል ።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባልና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሸና ማብራሪያ ሰጥተዋል ።
አቶ ሽመልስ በሰጡት ምላሽ፤ በለውጡ ዓመታት በሀገሪቱ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች አስደናቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ለዘመናት ስር ሰደው የቆዩ ችግሮችን በመፍታት ጠንካራና የበለጸገች ሀገር ለመገንባት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የሰላምና የኢንሸቲቭ ሥራዎች ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ከጋሞና ሌሎች አጎራባች ዞኖች ጋር የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንደሚጠናከር ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ባደረገችው እንቅስቃሴ አስደናቂ እመርታዎችን ማስመዝገቧን ጠቅሰው ህዝቡ የጉባ ብስራቶችን ጨምሮ ድህነትና ኋላቀርነትን ለማስወገድ በሚከናወኑ ተግባራት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ብልጽግና በመንግስት መሪነት እና በህዝቡ ትጋት የሚረጋገጥ በመሆኑ የሀገሪቱ ትልሞች እንዲሳኩ ህዝቡ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ፤ የመደመር መንግስት በየደረጃው የህዝቡን የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።
የክልሉን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የአከባቢን ፀጋ ከህዝብ ጋር በማስተሳሰር ለውጥ ለማምጣት በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከህዝቡ የተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።
በመድረኩ የፌደራል፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የጋሞ ዞን እና የአርባምንጭ ከተማ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።