አቅመ ደካማ ወገኖችንና የሀገር ባለውለታዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
አቅመ ደካማ ወገኖችንና የሀገር ባለውለታዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ አቅመ ደካማ ወገኖችንና የሀገር ባለውለታዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ 106 የቀበሌ ቤቶችን ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞችና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚኖሩ የሀገር ባለውለታዎች በእጣ አስረክበዋል።
በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክትም ከተማ አስተዳደሩ ለዘመናት የቆዩ ተደራራቢ ችግሮችን ለማቃለልና በድሕነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ለመደገፍ ሰው ተኮር ለሆኑ የልማት ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የዚህም ዋነኛ ዓላማ የዜጎችን አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታ ማሻሻልና ከተማዋን ማዘመን እንደሆነም ነው ያመለከቱት።
በመዲናዋ በተከናወኑ የሰው ተኮር የልማት ስራዎች እስካሁን ከ40 ሺህ በላይ የከተማዋ አቅመ ደካማ ወገኖችን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በመዲናዋ የሚከናወኑ ማህበራዊ የልማት ፕሮግራሞች ለነዋሪዎች ሰው ተኮር አገልግሎት በማቅረብ ረገድ ከተማ አስተዳደሩ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
በመዲናዋ የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽሉ የመኖሪያ ቤት ልማትና ሌሎች በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
መኖሪያ ቤት የተሰጣቸው ወገኖች በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ በሰው ተኮር ሥራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረጉ አመስግነዋል።