ቀጥታ፡

መንግስት ሁለንተናዊ ልማትን በማረጋገጥ እድገትን ለማፋጠን የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ቁርጠኛ ነን

ዲላ ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ):-መንግስት አሳታፊና ሁሉን አቀፍ ልማትን በማረጋገጥ የሀገርን እድገት ለማፋጠን የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ቁርጠኛ መሆናቸውን የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በዲላ ከተማ "የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተጠናቋል።


 

ነዋሪዎቹ በውይይቱ ላይ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በግብርናና ቱሪዝም ልማት፣ በማህበራዊ ዘርፍ፣ በአረንጓዴ አሻራ እንዲሁም በኮሪደርና በማዕድን ልማት ተጠቃሽ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።

የሌማት ትሩፋቱ በጌዴኦ ዞንና በዲላ ከተማም በተጨባጭ እየታየ መሆኑን አንስተው መንግስት አሳታፊና ሁሉን አቀፍ ልማት በማረጋገጥ የሀገርን አድገት ለማፋጠን እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

ይሁንና በሃይል አቅርቦት፣ በመንገድ መሰረተ ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በአርሶ አደር ማበረታቻና በቱሪዝም መዳረሻ ልማት ያሉ ውስንነቶች እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል። 


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሀገር ሽማግሌ ገብሩ ቀቀቦ፤ መንግስት እስከ ታች ወርዶ ህዝብን በማወያየት የሀገር እድገትን በጋራ ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በከተማው ህብረተሰቡን በማሳተፍ በኮሪደርና በመሰረተ ልማት ስራዎች፣ እንዲሁም በትምህርት ልማትና በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በተከናወኑ ስራዎች መሻሻሎች እንዳሉ አንስተዋል።

ይሁንና ከተማዋን ከወረዳ ጋር የሚያስተሳስሩ በፌደራልና በክልል መንግስት እንዲሁም በዞኑ አስተዳደር የተጀመሩ የመንገድ መሰረተ ልማቶች መዘግየታቸውን አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የሃይል አቅርቦት ውስንነት እንዳለ የገለጹት የሀገር ሽማግሌው፣ ችግሮቹ እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።

መንግስት አሳታፊና ሁሉን አቀፍ ልማትን በማፋጠን ሀገርን ለማሳደግ የጀመራቸውን ስራዎች እንደሚደግፉ ያነሱት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ ወይዘሮ ተረፈች ወራሳ ናቸው።


 

በተለይ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት፣ ገቢና ንግድ ዘርፎችን በማዘመን የተቀላጠፈ አገልግሎት እያገኘን ነው፤ ይህም ትልቅ ለውጥና ውጤት በመሆኑ በሌሎችም ዘርፎች መጠናከር አለባቸው ብለዋል።

መንግስት ህብረተሰቡን በማስተባበር የትምህርት ስብራትን ለመጠገን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ምቹ የመማሪያ አካባቢ መፍጠሩን ያነሱት ደግሞ መምህር ፈለቀ አየለ ናቸው።


 

የኑሮ ጫናን ለመቀነስ የደመወዝ ማሻሻያ መደረጉን በመልካምነት አንስተው፣ በከተማው በተማሪዎች ምገባ፣ በመጻህፍት አቅርቦትና በመምህራን ልማት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሀገራዊ የልማት ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑና ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ያነሱት ደግሞ አቶ ከበደ ዱሌ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።


 

በሥራ እድል ፈጠራ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ጠቅሰው በተለይ በዲላና ይርጋጨፌ ከተሞች የተገነቡ አግሮ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ ጠይቀዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግስት በልማትና በመልካም አስተዳደር ላይ የተነሱ ጥያቄዎች ተቀብሎ በየደረጃው ምላሽ ለመስጠት ይሰራል ብለዋል።


 

ሁሉንም የልማት አቅሞች በመደመር ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን የህብረተሰቡ የላቀ ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም የጉባ ብስራቶችን ከግብ ለማድረስ ህብረተሰቡ በየአካባቢው ሰላሙን ከመጠበቅ ባለፈ የጀመረውን የልማት ተሳትፎ ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የባህር በር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አስኳል መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ  ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ በባዳዎችና ባንዳዎች እንዳይደናቀፍ ውስጣዊ አቅም ማጠናከር አለብን ብለዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው፤ ጌዴኦ ከሰው ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ የሚኖር ሠላም ወዳድ ህዝብ መሆኑን አንስተዋል።


 

ይህም ትልቅ ባህላዊ እሴት መሆኑንን ገልጸው በአካባቢው ያለውን የተፈጥር ሀብት በማልማት ለወጣቶች የሥራ እድልና ለሀገራዊ እድገት ለማዋል ይሰራል ብለዋል።

የለውጡ መንግስት ወደስልጣን ከመጣ ጊዜ አንስቶ ያለምንም ልዩነት የልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እየመለሰ መሆኑንና ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በመድረኩ በተለያዩ የልማት ዘርፎች እንዲፈቱ ለቀረቡ ጥያቄዎች በቀጣይ ምላሽ በመስጠት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም