ቀጥታ፡

በድሬዳዋ አስተዳደር የተከናወኑና በሂደት ላይ ያሉ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር የተከናወኑና እየተከናወኑ የሚገኙ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ተናገሩ።

"የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሃሳብ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ከክልሎችና ከአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።


 

በውይይቱ የተሳተፉ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች እንዳሉት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በድሬዳዋ የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ለህዝቡ መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ በመሆኑ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ቃልኪዳን ፍስሃ እንዳለችው፤ በለውጥ ዓመታቱ የማህበረሰቡን የልማት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።

የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ተግባራትን ለማስቀጠል በተደመረ መንገድ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ተናግራለች።

የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነትና የአመራር ሚናን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን ያነሱት ደግሞ ወይዘሮ አኒሳ አብዱረህማን ናቸው።

በድሬዳዋ በመንገድና በኮሪደር ልማት ግንባታ፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በኢንዱስትሪ እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ልማቶች ተጨባጭ ውጤት ያስገኙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

መላከ ህይወት ቀሲስ አፈወርቅ አስፋው በበኩላቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ያረጋገጡት የሰላም እና ልማት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።


 

የኃይማኖት አባቶችም ሰላምን፣ መደጋገፍንና ልማትን በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የልማት ፕሮጀክቶቹ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ቢሆንም የመልካም አስተዳደር፣ የሥራ አጥነት እንዲሁም የኑሮ ውድነት ተጨማሪ ጥረትና ስራ ይጠይቃል ያለው ደግሞ ወጣት ሊበን ጣሂር ነው።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አበራ አንጋሱ የትውልዱ ቁጭት ሆኖ የቆየው የባህር በር ጥያቄ ወደ አጀንዳ መምጣቱ ትልቁ እርምጃ ነው ብለዋል።

የለውጡ መንግስት ህዝብን በማስተባበር ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠናቆ ለህዝብ ጥቅም እንዳዋለ ሁሉ በአሁኑ ወቅት የተጀመሩት ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችም ከዳር እንዲደርሱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አክለዋል።

ህዝባዊ ውይይቱን የመሩት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስተዳደሩ ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት የተገበራቸው ስራዎች የብልፅግና ጉዞን ለማሳካት ከፍተኛ እቅም አላቸው ብለዋል።


 

እነዚህን ዘርፈ ብዙ ልማቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በፍጥነትና በፈጠራ በመታገዝ ይበልጥ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይም በሌማት ትሩፋት እና ሌሎች ኢንሼቲቮች የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር የወጣቱን የስራ ዕድል ጥያቄ የመመለስና የህብረተሰቡን ገቢ የማሳደግ ስራ እንድሚሰራ ገልጸዋል።

የጋራ ገቢ ክፍፍል፣ የገበታ ለሀገርና መሰል የልማት ኢንሼቲቮች ድሬዳዋ ላይ እንዲተገበሩ ከነዋሪዎች የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በትኩረት ይሰራል ያሉት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) ናቸው።

የድሬዳዋ ነዋሪዎች የሀገርን የብልፅግና ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ በህብረ ብሔራዊ አንድነት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በውይይቱ ከህዝብ የቀረቡ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ በየደረጃው የሚገኘው አመራር የሃሳብና የተግባር አንድነቱን አጠናክሮ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም