በመንግሥት እና ሕዝብ ቅንጅት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጐልበት ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገር ለማስረከብ እንሰራለን - ኢዜአ አማርኛ
በመንግሥት እና ሕዝብ ቅንጅት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጐልበት ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገር ለማስረከብ እንሰራለን
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ በመንግሥት እና ሕዝብ ቅንጅት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጐልበት ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገር ለማስረከብ እንደሚሰሩ በጅማ ሕዝባዊ መድረክ የተሳተፉ ነዋሪዎች ገለጹ።
"የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች " በሚል መሪ ሀሳብ ከጅማ ዞን እና ከጅማ ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
በመድረኩ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፣ በብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ነመራ ቡሊ፣ የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቲጂኒ ናስር እና ከጅማ ዞን እና ከተማ የተወጣጡ ተሳታፊዎች ታድመዋል።
በጅማ ሕዝባዊ ውይይት የተሳተፉ ነዋሪዎች ባነሱት ሀሳብ እንደገለጹት፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ አስደናቂ የልማት ስኬቶች ተመዝግበዋል።
በጅማ እየተከናወኑ የሚገኘው የከተማ ልማት፣ የግብርና ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች መሆናቸውን ነው የገለጹት።
በዚህም የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን በማድረግ ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ የተያዙ ግቦች ስኬታማ መሆናቸው ተጠቁሟል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ፤ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ዕውን የሚያደርጉ ተጨባጭ የልማት ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና በዲጂታል እንዲሁም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በከተማ ልማት ዘርፎችና በሌሎችም አመርቂ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር) የተበሰሩ የጉባ ብሥራቶች የኢትዮጵያን ማንሰራራት ዕውን የሚያደርጉ እና የሀገርን ዕድገት ማፋጠን የሚያስችሉ ናቸውም ብለዋል።
ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሣሌት ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ውጤታማ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የውስጥ ባንዳ እና የውጭ ባዳ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ማስቆም አይችሉም ብለዋል።
በመደመር መንግሥትና ሕዝብ ቅንጅት የተገኙ ትላልቅ ድሎችን እያጣጣምን ለበለጠ ስኬት መዘጋጀት ይገባል ብለዋል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ ጠሃ ቀመር ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሑፍ፤ በጅማ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የሕዝቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በከተማ ልማት፣ በመሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ ሕዝቡን የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ከማረጋገጥ አኳያ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በቅርበት ለመመለስ በርካታ የቀበሌ አስተዳደር መደራጀቱን ጠቁመው፤ ከጸጥታ አኳያም ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የኑሮ ውድነት ጫናን ለማቃለል፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማዘመንና የመሠረተ ልማቶችን ይበልጥ ለማስፋፋት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመዋል።
በጅማ ሕዝባዊ ውይይት የተሳተፉ ነዋሪዎች ባነሱት ሐሣብ፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ መንግሥት አስደናቂ የልማት ስኬቶች ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
በጅማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ፣ በግብርና ልማት በስንዴ፣ በሻይ እንዲሁም በሩዝ ምርት ዘርፎች ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሴራ ያጣችውን የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመው፤ ትውልዱ ይበልጥ እንዲረዳውም በትምህርት ቤቶች የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
በቀጣይ መሠረተ ልማትን ይበልጥ ለማስፋፋት፣ የኑሮ ውድነትን ጫናን ለማቃለል፣ አገልግሎት አሠጣጥን ይበልጥ ለማሣለጥ እንዲሁም የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎቹ እንዲገነቡላቸው ጠይቀዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ነመራ ቡሊ በሰጡት ሐሳብ፤ የኑሮ ውድነት ጫናን ለማቃለል ምርታማነትን ለማሣደግ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው፤ በሌማት ትሩፋትና በከተማ ግብርና ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የቀበሌ አደረጃጀት በሁሉም አካባቢዎች መዘርጋቱን ጠቁመው፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ በአምስት ከተሞች የማደራጀት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ ጃንጥራር አባይ ፤ መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ትርጉም ባለው መልኩ ማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
መንግሥት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በከተማ ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በማህበራዊ ልማት ዘርፎች እና በሌሎችም የልማት አብዮት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በመድረኩ የተነሱ ሀገራዊ የጋራ ትርክትን ማሣደግ የሚያስችሉ እንደ ባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ የመሳሰሉ ሀሳቦች የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ያግዛሉ ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የታሪክ እጥፋትና የመደመር መንግሥት ቁርጠኝነትን በተግባር ያሳየ መሆኑን በጅማ ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይ ተንጸባርቋል።