በለውጡ ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ እመርታዊ ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በለውጡ ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ እመርታዊ ውጤቶች ተመዝግበዋል
አዳማ ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ):-በለውጡ ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ እመርታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
''የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች'' በሚል መሪ ሀሳብ የአዳማ ከተማና ምስራቅ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች የተሳተፉበት ህዝባዊ ውይይት መድረክ ተካሄዷል።
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በለውጡ ዓመታት በተለይም የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በግብርና ልማትና በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የተመዘገቡ ስኬቶችን አንስተዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ሸምበል ተመስገን ኃይለማርያም፤ በአዳማ ከተማ የተከናወኑ የልማት ፕሮጀከቶች ከተማዋን የለወጡ እና ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ስራው የአደማ ከተማን አጠቃላይ ገጽታ የቀየረ፣ የነዋሪውንም ተጠቃሚነት ያሳደገ መሆኑን ገልጸው ለቀጣዩ ትውልድ መሰረት ያኖረ ዘመናዊ የከተማ ልማት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በግብርና ልማትን ስንዴን ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም የሌማት ትሩፋት የብዙዎችን ህይወት የቀየረ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በለውጡ ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉና እመርታዊ ውጤት የተመዘገበባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የባህር በር ማጣት የሀገር የህልውና ጉዳይ አድርጎ በመያዝ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን የተጀመረው ጥረትም ትልቅ ተስፋ የሰነቅንበት ነው ብለዋል።
የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች ቢሆንም በቀጣይ ብዙ መስራት የሚጠይቅ በመሆኑ የህዝብና መንግስትን ጠንካራ ጥረት ይጠይቃል ሲሉም አንስተዋል።
ሌላኛዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ዘቢባ ከድር፤ በለውጡ ዓመታት የመጡ ተጨባጭ ውጤቶችን እውቅና መስጠትና የሚታዩ ክፍተቶችን ማስተካከል የጋራ ስራችን መሆን አለበት ብለዋል።
በመሆኑም በለውጡ ዓመታት የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች እጅግ የሚበረታቱ እና ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይ በተለይም የኑሮ ውድነትን መቀነስ እና የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር መፍታት ይገባል ብለዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለመማሪያ መፅሐፍ አቅርቦት ትኩረት መሰጠት አለበት ሲሉም አንስተዋል።
ከምስራቅ ሸዋ ዞን ቦራ ወረዳ ውይይት ላይ የተሳተፉት አቶ ተሾመ አበራ፣ በለውጡ ዓመታት እምቅ ሃብቶችን በማልማት ከተረጂነት ለመውጣት የስንዴ ልማትን ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።
ከአዳማ ከተማ ወንጂ ወረዳ አቶ ከበደ ዘርጋው፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታን አጠናቀን የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ልማትና የባህር በርን ለመስመለስ የተጀመሩ ስራዎች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፣ በግብርና ዘርፍ ስንዴ፣ ሩዝና ሌሎች ኢንሼቲቮችን ውጤታማ በማድረግ የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጡ ስራ የመንግስት ወሳኝ አጀንዳ ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።
በዲጂታል አገልግሎት፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በተደረገው ጥረትም አበረታች ውጤት መገኘቱን አንስተው በቀጣይም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል።
የዛሬው የውይይት መድረክም ለህዝብ የተገባው ቃልና የተፈፀሙ ስራዎች ያሉበትን ደረጃ ለማየትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ መሆኑን ገልጸዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሣ በበኩላቸው፤ በአዳማ ከተማ እየታየ ያለው ፈጣን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህብረተሰቡ ተሳትፎውን ማጠናከር አለበት ብለዋል።
የግብርና ምርትን እሴት ተጨምሮበት ለገበያ ለማቅረብ ትኩረት መደረጉን ያነሱት ሚኒስትሯ በሁሉም የልማት መስኮች የወጣቶችን እምቅ አቅም በስፋት መጠቀም ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ፤ በአዳማ ከተማና ምስራቅ ሸዋ ዞን ሰላም በማስፈን የህዝቡ የልማት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት እንዲስፋፋ ይሰራል ብለዋል።