ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን የመኽር ሰብል የመሰብሰብ ሂደት ተጠናክሮ ቀጥሏል

ደብረ ማርቆስ ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ):- በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን የመኽር ሰብል የመሰብሰብ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የዞኑን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አበባው እንየው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የደረሰውን ሰብል ብክነትን በሚያስቀር  መልኩ  የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ ነው።


 

የሰብል አሰባሰቡ ኮምባይነርን ጨምሮ በደቦ፣ በልማት ቡድን አደረጃጀት እና ሌሎችም አማራጮች እየተከናወነ መሆኑን አስታውሰዋል።

በዚህም በመኽር ወቅቱ በሰብል ከተሸፈነው 640 ሺህ ሄክታር እስካሁን ከ300 ሺህ ሄክታር በላይ የደረሰ ሰብል ተሰብስቧል ብለዋል።

የቀረውም ሰብል በቀጣይ ጥቂት ቀናት ተሰብስቦ የሚጠናቀቅ መሆኑን ገልጸው በመኽር ከለማው ሰብል ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት የሚገኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአነደድ ወረዳ የጃማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ምህረት በቃሉ እና በባሶሊበን ወረዳ የልምጭም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታደገ ልየው፤ በመኽር ያዘመሩትን የጤፍ፣ የስንዴ፣ የበቆሎ እና ገብስ ሰብሎችን መሰብሰባቸውን ገልጸዋል።


 

በመንግስት በተደረገላቸው እገዛ የምርት ብክነትን በሚያስቀር መልኩ ሰብላቸው መሰብሰቡን አስታውሰው ከበፊቱ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙም ተናግረዋል።

‎በአማራ ክልል በመኽሩ ከለማው 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም