ከተማ አስተዳደሩ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን እያከናወነ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ከተማ አስተዳደሩ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን እያከናወነ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማ አስተዳደሩ በልደታ ክፍለ ከተማ 106 የቀበሌ ቤቶችን ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አቅመ ደካሞች፣ የአካል ጉዳተኞችና የሀገር ባለውለታዎች ለሆኑ እና እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎችን በመለየት ዛሬ በእጣ ማስተላለፉን ጠቁመዋል።
አስተዳደሩ ከህዝብ ጋር በተደረገ ውይይት የተሰጡ ጥቆማዎችን ጭምር ተጠቅሞ ባደረገው ማጣራት ነዋሪዎቹ መለየታቸውን አንስተዋል።
በዚህም ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ የተዘነጉ፣ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አቅመ ደካማ ወገኖችን እንባ በማበስና ከነበሩበት አስከፊ ሕይወት በመታደግ ነገን በተስፋ እንዲያዩ የሚያስችል ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
በተለይም ከአራዳ ክፍለ ከተማ ከቁርጡሚ ወንዝ ዳርቻ ተነስተው በሶስተኛ ወገን ክርክር ምክንያት ሲንገላቱ የቆዩ ነዋሪዎች ዛሬ ችግሩ ተፈቶ የመኖሪያ ቤት ስላገኙ እጅግ ደስተኞች ነን፤ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል ከንቲባዋ በመልዕክታቸው።