የጤና ተቋማትን በማስፋፋት ለዜጎች የህክምና አማራጭ ማቅረብ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ተቋማትን በማስፋፋት ለዜጎች የህክምና አማራጭ ማቅረብ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ጤና ሚኒስቴር
ጅማ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ የጤና ተቋማትን በማስፋፋት ለዜጎች የህክምና አማራጭ ማቅረብ የሚያስችሉ ትግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተገነባ የዓይን ባንክ ማዕከል የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የጤና ተቋማትን በማስፋፋት ዜጎች የሕክምና አማራጭ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
የተገነባው የዓይን ባንክ ማዕከል የዓይን ሕክምና ለሚሹ ወገኖች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት የሚፈጠርን የእይታ ችግር ለማከም ማዕከሉ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ፕሮፌሰር ነፃነት ወርቅነህ በበኩላቸው፤ ቢሮው የጤና ተቋማትን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተገነባው የዓይን ባንክ ማዕከልን ለማቋቋም ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው፤ ተቋሙ የዓይን እክል ችግር አሳሳቢነትን በመረዳት የሕክምና ማዕከላትን ለማስፋፋት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዓይን ባንክ ማዕከሉ ለብዙ ወገኖች ለዓይን ሕክምናው ተደራሽ በማድረግ ረገድ ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።
ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የዓይን ባንክ ማዕከል ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ አገልግሎት እና የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ በመተባበር መገንባቱን አንስተዋል።