ቀጥታ፡

የአረካ ከተማ ኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ቀይሯል - ነዋሪዎች

አረካ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ በወላይታ ዞን አረካ ከተማ የተከናወነው የተቀናጀ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ነዋሪዎች ተናገሩ።


 

ልማቱን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪ ታከለ ጊንጆ እንደገለጹት የኮሪደር ልማት ከዚህ ቀደም ቆሻሻ መጣያ የነበሩ ሥፍራዎችን በማልማት የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ለእይታና ለኑሮ ምቹ አድርጓል።

በሌሎች ከተሞች አይተው ሲመኙት የነበረው የኮሪደር ልማት በከተማቸው በመጀመሩ መደሰታቸውን ጠቅሰው፣ ልማቱ የፈጠረው ምቹ ሁኔታ ወደ ሌሎች ከተሞች ከማማተር ይልቅ ትኩረታችንን እዚህ እንዲሆን አድርጓል ብለዋል።


 

ሌላው አስተያየት ሰጪ መሐመድ አብደላ በበኩላቸው የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ አረንጓዴ ሥፍራዎችና የመዝናኛ አማራጮች እንዲስፋፉ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረው፣ ልማቱ ለብዙዎች የመዝናኛ እና የሥራ ዕድል መፍጠር አስችሏል ነው ያሉት።


 

ኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገድ፣ የመንገድ ዳር መዝናኛና የተለያዩ ግንባታዎችን አካቶ መከናወኑን የተናገሩት የአረካ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የማስፈጸም ዘርፍ ኃላፊ መለከት ማርቆስ ናቸው።

ልማቱ በማህበር የተደራጁ ወጣቶችም ወደ ሥራ ገብተው አቅማቸውን እንዲያወጡና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል መፍጠሩን በመግለጽ።


 

በኮሪደር ልማት የከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማፋጠንና የነዋሪውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአረካ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከበደ ካሳ ናቸው።

በዚህም በመጀመሪያና በሁለተኛ ዙር 2 ነጥብ 5ኪ.ሜ የኮሪደር ልማት ሥራ መከናወኑንና በማህበር የተደራጁ ዜጎችም በኮሪደር በለሙ አካባቢዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በከተማው የኮሪደር ልማት ሥራ በተለያየ ምዕራፍ ተከፋፍሎ እየተከናወነ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅትም በከተማው አራዳ ቀበሌ ከ18 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ሦስተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

ህብረተሰቡ ለኮሪደር ልማቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ የለሙ አካባቢዎችን በመንከባከብና በመጠበቅ በኩል የማስገንዘብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም