በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እስካሁን ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እስካሁን ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል
ጎንደር፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እስካሁን ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
በመምሪያው የመስኖ ልማት ቡድን መሪ ሃውልቱ ታደሰ፤ አርሶ አደሩ ከበጋ የስንዴ መስኖ ልማቱ በተጓዳኝ ሌሎችንም ሰብሎች በመስኖ በማልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በዞኑ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 28ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።
የታየዘውን ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ዘንድሮ በመስኖ ከሚለማው ስንዴ ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
በዞኑ ለመስኖ ልማት ስራ ከ5 ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ጨምሮ የአፈር ማዳበሪያና የዘር አቅርቦት መኖሩን ገልጸዋል።
አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች እየተስፋፉ መሆኑን አንስተው የልማት ስራው በልዩ ትኩረትና በቅንጅት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዘርፉ ልማት ከተሰማሩት አርሶ አደሮች መካከል ምትኩ በላይ እና ጌትነት መርሻ፤ በመንግስት ልዩ ትኩረትና በባለሙያዎች እገዛ የልማት ስራው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመስኖ መልማት የሚችል ከ100ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መኖሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ መረጃ ያመለክታል፡፡