ቀጥታ፡

በክልሉ የኮደርስ ስልጠና መርሐ ግብር በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ነው

ሚዛን አማን ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ):- የኮደርስ ስልጠና መርሃ ግብር በተጠናከረና በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ አስታወቀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ለ5 ሚሊዮን ዜጎች ነፃ የኮደርስ የስልጠና እድል በመመቻቸቱ እስካሁን በርካቶች የእድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስፋው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ 138 ሺህ ዜጎችን ለማሰልጠን ዕቅድ የተያዘ ሲሆን ከእነዚህም መካከል እስካሁን 16 ሺህ 700 የሚሆኑት ስልጠናውን አጠናቀው የምሥክር ወረቀት አግኝተዋል።

በተያዘው ዓመትም የስልጠናው ሂደት ተጠናክሮ የቀጠለ በመሆኑ ተጨማሪ 63 ሺህ ዜጎችን የማሰልጠን እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የስልጠናው ዓላማ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ማፍራት መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው የእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ጊዜ ሳያባክኑ መመዝገብና መሰልጠን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ሥልጠናውን ወስደው ሰርተፊኬት ከተቀበሉት መካከል የሲዝ ከተማ አስተዳደር ነዋሪው ወጣት ምናሉ ግዛቸው፤ በሥልጠናው ከዘመኑ ጋር ተወዳዳሪ እንድሆን የሚያስችለኝን እውቀት አግኝቻለሁ ብሏል።


 

በወሰዳቸው አራት ኮርሶች ከመሠረታዊ የኮምፒዩተር እውቀት ጀምሮ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ እና ፕሮግራሚንግ ላይ በቂ ክህሎት ማግኘቱን ተናግሯል።

የሥልጠና አሰጣጥ ሁኔታው ቀላልና ለመያዝ ምቹ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ጊዜ ብቻ ሰጥቶ ዕድሉን መጠቀም እንዳለበት ነው የተናገረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም