የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ምልክት የሆነው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ምልክት የሆነው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር
የኢትዮጵያ ዋንጫ በ1937 ዓ.ም የተጀመረ አንጋፋ የጥሎ ማለፍ ውድድር ነው። ውድድሩ በወቅቱ የነበረውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር (አሁን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ) ለመደገፍ ነበር።
የጥሎ ማለፍ ውድድር ፎርማት የሆነው የኢትዮጵያ ዋንጫ እንደ እንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ እና በሌሎች ሀገራት ከሚደረጉ ውድድሮች ተመሳሳይነት ያለው ነው። በውድድሩ የመጀመሪያ ዓመታት ላይ ይሳተፉ የነበሩ ክለቦች በአዲስ አበባ እና ዙሪያ የሚገኙ ክለቦች ናቸው።
የእግር ኳስ መዋቅሮችን ለመዘርጋት እና ሀገር በቀል አቅምን ለመለየት የመጀመሪያ ዓመታት ውድድሮች ወሳኝ ሚና ነበራቸው። በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1950ዎቹ እና 1960ዎቹ ላይ የኢትዮጵያ ዋንጫ በጊዜ ሂደት እየሰፋ በመምጣት ብሄራዊ እውቅናን ያገኘ ሲሆን በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች የሚገኙ ክለቦች በስፋት መሳተፍ ጀመሩ።
ውድድሩ የብሄራዊ አንድነት መገለጫ እና መሳሪያ መሆንም ችሏል። የእግር ኳስ መሰረተ ልማት እያደገ መምጣት በተለይም የስታዲየሞች እና የልምምድ ስፍራዎች መስፋት የሊግ ውድድሮች ለኢትዮጵያ ዋንጫ እድገት የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል።
በታህሳስ ወር 1928 ዓ.ም የተመሰረተው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ውድድሩን ለበርካታ ጊዜያት በማንሳት የበላይነቱን ይዟል። ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1970ዎች እና በ1980 ዎቹ የመንግስት እና የንግድ ድርጅቶች መሳተፍ የጀመሩበት ወቅት ነው። ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ (በድሮ አጠራሩ መብራት ሃይል)፣ እርሻ ሰብል፣ ኢትዮ ሲሚንቶ፣ መቻል እና ኢትዮጵያ መድን ከተሳታፊዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
1970ዎች እና በ1980ዎቹ የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር የበለጠ ቅርጽ እየያዘ እና እየተዋቀረ የመጣበት ወቅት ነው። የመርሃ ግብሮች የጊዜ ሰሌዳ፣ ሽልማት ክፍፍል እና የዳኝነት አሰራሩ መሻሻል ያሳየበት ነው። የመገናኛ ብዙሃን የዘገባ ሽፋን መስፋትም ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቁልፍ ስፖርታዊ ሁነት እንዲሆን አስችሎታል።
በኢትዮጵያ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ዋንጫ ከካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ (ካፍ) ውድድሮች ጋር በማስተሳሰር ክለቦች በአህጉር አቀፍ ደረጃ የመሳተፍ እድል እንዲያገኙ አስችሏል። በ199ዎቹ እና በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ከሁለት ሺህ በኋላ የኢትዮጵያ ዋንጫ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የስፖርት አፍቃሪ በስታዲየም ገብቶ የሚመለከተው እና ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ያገኘ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ዋንጫ የሚያሸንፉ ቡድኖች የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ በመሆን ይሳተፋሉ። የኢትዮጵያ ዋንጫ በተለያዩ ምክንያቶች በተለያዩ ጊዜያት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም አሁንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ምልክት ሆኖ ቀጥሏል። ውድድሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባህል እና እድገት መለኪያ መሆን የቻለ ሲሆን በዜጎች መካከል የእርስ በእርስ ትብብርን በመፍጠር ረገድ የበኩሉን ሚና ተወጥቷል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ሲነሳ የኢትዮጵያ ዋንጫን አለማንሳት አይቻልም።
መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያን ዋንጫ በብዛት ማንሳት ስኬታማው ክለብ ናቸው። ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ እርሻ ሰብል፣ አዳማ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሲዳማ ቡና፣ ሃዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ሌሎች የኢትዮጵያ ዋንጫን ካነሱ ክለቦች መካከል ይጠቀሳሉ።
የኢትዮጵያ ዋንጫ ሶስተኛ ዙር መርሃ ግብር ከታህሳስ 4 እስከ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
ቅዳሜ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከነጌሌ አርሲ ከረፋዱ አራት ሰዓት፣ ባህር ዳር ከተማ ከቦዲቲ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት እና ኢትዮጵያ መድን ከቢሾፍቱ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በአዲስ አበባ ስታዲየም መቻል ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
መርሃ ግብሩ እሁድም ቀጥሎ ሲውል ደብረ ብርሃን ከተማ ከቤንች ማጂ ቡና በአዲስ አበባ ስታዲየም እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከንብ እግር ኳስ ክለብ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተመሳሳይ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ሲዳማ ቡና ከአርባ ምንጭ ከተማ በአዲስ አበባ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ ይጫወታሉ ።
ሰኞ ታህሳስ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ ቡና ከመቀሌ 70 እንደርታ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሶስተኛው ዙር የሚያሸንፉ ክለቦች ለሩብ ፍጻሜ ያልፋሉ። የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ወላይታ ድቻ በአንደኛው ዙር መሰናበቱ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዋንጫን የሚያሸንፈው ቡድን በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ይሳተፋል።