ቀጥታ፡

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ትርክቶችን መቅረጽ ይጠበቅባቸዋል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፡- የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ፣ ሀገራዊ አንድነትንና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ትርክቶችን መቅረጽና ማስረፅ እንደሚጠበቅባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ።

በኪነ-ጥበብ እና ስነ-ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ የተዘጋጀ የጥበባትና ፈጠራ ኢንዱስትሪ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው።

በመድረኩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።

ባዳ እና ባንዳ የጋራ ግባቸው ኢትዮጵያን ማዳከም መሆኑን ገልጸው፥ የጠላት ኢላማዎች ዓባይ፣ የባህር በር፣ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬያችን፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን እና ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነታችን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በጂኦ ስትራቴጂያዊ ቁመናቸው ከታደሉ የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነች በማንሳት፥ ይህንን ጂኦፖለቲካዊ ቁመና ለመለወጥ በኢትዮጵያ ላይ የቴክኖሎጂ፣ አካላዊ እና የትርክት ጦርነት ተካሂዶባታል ብለዋል።

በእነዚህ ጦርነቶቾ ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ የባህር በር እንድታጣ መደረጉን እና አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ የደህንነት ተጋላጭነቷ መስፋቱንም አንስተዋል።

ከዓለም አቀፉ የንግድ መስመር በማራቅ ኢኮኖሚዋንና ሁለንተናዊ ብሔራዊ አቅሟን በማዳከም በውስጥ ጉዳይ ብቻ እንድትተራመስ ጠላቶቿ ተግተው መስራታቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በብሔራዊ ጥቅም የማይደራደር ዜጋ ለመፍጠርና የትርክት ጫናን ለመመከት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።


 

ሀገራዊ ለውጡ የጠላት ኢላማ ለሆኑት ዓባይ፣ የባህር በር፣ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እና ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነት ትኩረት በመስጠት ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አበራርተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ሪፎርሞችን በማድረግ፣ ብሔራዊ ጥቅሟን በማስጠበቅ፣ ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነት በመፍጠር ጠንካራ ኢኮኖሚ እና የጸጥታ ተቋማት ግንባታ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ብሔራዊ አሰባሳቢ ትርክት ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ትልቁ መሳሪያ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አንድነትን፣ አብሮነትን እና እድገትን የሚያረጋግጡ ትርክቶችን መቅረጽ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም