የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በዘላቂነት ለመቀየር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በዘላቂነት ለመቀየር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በዘላቂነት ለመቀየር የሚከናወኑ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የምግብ ዋስትና(ሴፍቲኔት) ተጠቃሚ ለነበሩ ዜጎች በአራት ክፍለ ከተሞች የተገነቡ የማምረቻና መሸጫ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን አስረክበዋል።
ከንቲባዋ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት ከተማ አስተዳደሩ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና በምግብ ዋስትና (ሴፍቲኔት) ፕሮግራም ተጠቃሚ የነበሩ ዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ከዚህ ውስጥም ዛሬ ለተጠቃሚዎች የተላለፉት የመስሪያና መሸጫ ቦታዎች ነዋሪዎቹን ከተረጂነት ወደ አምራችነት የሚያሸጋግሩ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
በአጠቃላይ እስካሁን ከአምስት መቶ ሃያ ሺህ በላይ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ወደ ተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንዲሸጋገሩ በማድረግ በዘላቂነት ሕይወታቸው እንዲቀየር የማድረግ ሥራ መሰራቱን አስታውቀዋል።
በቀጣይም በሴፍቲኔት የታቀፉ ዜጎችን ኑሯቸውን በዘላቂነት እንዲያሻሽሉ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዛሬው እለት የመስሪያ ሕንፃዎቹን የተረከቡት ተጠቃሚዎች በርትተው በመስራት የራሳቸውን ሕይወት ከመቀየር ባለፈ ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን ማቲዎስ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ከተማ አስተዳደሩ ዜጎች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ሃብት እንዲያፈሩ እያደረገ ነው።
በዋናነትም የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ ሥልጠናዎች እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት በአዲስ ከተማ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በየካ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች የተገነቡ ሕንፃዎች የሴፍቲኔት ፐሮግራም ተጠቃሚዎች ለነበሩ ዜጎች መተላለፋቸውን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በዛሬው ዕለት 292 ኢንተርፕራይዞች እና 976 የቤተሰብ ወኪሎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አክለዋል።
በተያያዘም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት አስረክበዋል።