ቀጥታ፡

ለመደመር መንግስት እሳቤዎች ተግባራዊነት ሚናችንን እንወጣለን 

ወልዲያ/ገንዳውሃ ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ):-የመደመር መንግስት ዕይታና እሳቤዎች ብልፅግናን ለማረጋጋጥ የሚያስችሉ በመሆናቸው ለተግባራዊነታቸው ሚናቸውን  እንደሚወጡ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ። 

የመደመር መንግስት እሳቤዎች  ብዝሃ ኢኮኖሚን በመገንባት ለብልፅግና ጉዞ መሳካት ከፍተኛው የእድገት  ምሰሶ እንደሆኑ  ተገልጿል። 

በተለይም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂና መሰል ዘርፎች የተሰጠው ትኩረት ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑ ተመልክቷል። 

በሰሜን ወሎና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ኢዜአ ያነጋገራቸው የመንግስት ሰራተኞች፤  በመደመር መንግስት እሳቤ መሰረት የአካባቢያቸውን ፀጋ ለይተው ልማት ላይ እንዲያውሉ  በማመቻቸት እድገት እንዲፋጠን እንደሚሰሩ ገልጸዋል። 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል እሴቶች ባለሙያ አቶ ግዛው መኩሪያው፤    በመደመር መንግስት  የብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፎችን በጊዜ የለኝም መንፈስ በመስራት ሃገራዊ እድገትን ማፋጠን ይገባናል ብለዋል። 


 

እንደ ሰሜን ወሎ ዞን ያለውን የቱሪዝም  እምቅ ሃብት በማስተዋወቅና በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሁሉ ሚናቸውን እንደሚወጡ  አረጋግጠዋል። 

በዞኑ አስተዳደር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ታደሰ አብዬ በበኩላቸው፤ የተያዙ ዘርፈ-ብዙ እቅዶችን በመደመር እሳቤ ለማሳካት ቁርጠኛ ሆነን ልንሰራ ይገባል ብለዋል። 


 

በመሆኑም ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ የትምህርትና የጤናው ዘርፍ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲታገዙ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። 

የመደመር መንግስት ዕይታ ብልፅግናን ለማሳካት የሚያስችሉ ጥልቅ እሳቤዎች በመሆናቸው ለስኬታማነታቸው ተግተን እንሰራለን ያሉት ደግሞ የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ማንደፍሮ ጌታልጅ ናቸው። 

ሕብረተሰቡ የመደመር መንግስት እይታዎችን በውል ተገንዝቦ ወደ ተግባር እንዲለወጡ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን በኩል የጋራ መግባባት ስራዎችን በትኩረት እናከናውናለን ብለዋል።

በተመሳሳይ የምዕራብ ጎንደር ዞን የመንግስት ሰራተኞች ፤ የመደመር መንግስት እሳቤ ከሀገር በቀል እውቀት በመመንጨት ብልፅግናን ለማረጋገጥ ምቹ  ሁኔታ መፍጠሩን  ገልጸዋል። 

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ እርጥባን መስፍን እንዳሉት፤ የመደመር መንግሰት እሳቤ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ  ነው። 


 

ኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮ ሀብትን ጨምሮ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ታሪካዊ ሀብቶች ያሏት ሀገር ናት ያሉት አቶ እርጥባን፤  ይህን ሀብት አውጥቶ በመጠቀምና በማልማት ጥቅም ላይ እንዲውል የመደመር መንግስት አሻራ ማስቀመጡን ተናግረዋል። 

በዞኑ የገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ገብረ ኪዳን መንጋው በበኩላቸው፤ የመደመር መንግስት ሰላምና ልማትን ሳይነጣጥል በመስራት ለሌሎች ምሳሌ የሆነ እሳቤ መሆኑን ገልፀዋል። 


 

እሳቤው በመፍጠንና መፍጠር ላይ ባለው የፀና አቋም በኢትዮጵያ ሊሳኩ አይችሉም የተባሉ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት በመፈፀም ህዝባዊና አለም አቀፋዊ እውቅና ያገኘ መሆኑንም ተናግረዋል። 

የመደመር መንግስት እሳቤዎች ብልፅግናን ለማረጋጋጥ የሚያስችሉ በመሆናቸው ለተግባራዊነታቸው  ሚናቸውን  ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ  ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም