የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከፍተኛ እድገትና ማንሰራራት እያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከፍተኛ እድገትና ማንሰራራት እያሳየ ነው
ሐረር፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ በለውጡ ዓመታት በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ከፍተኛ እድገትና ማንሰራራት እያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) ገለጹ።
የፌዴራል፣ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የኢንቨስትመንት አስፈፃሚዎች የጋራ ምክክር መድረክ በሐረር ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር)፤ ባደረጉት ንግግር በዘርፉ የነበረውን ችግር በመፍታት እመርታ ለማምጣት ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በለውጡ ዓመታት ለሀገር ውስጥና ለውጪ ባለሀብቱ ምቹና ተገማች የኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው በዚህም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ከፍተኛ እድገትና ማንሰራራት እያሳየ ይገኛል ብለዋል።
በለውጡ ዓመታት ከ130 በላይ የህግ፣ አዋጆች፣ መመሪያዎችና ሌሎች አሰራሮችን የመለወጥ ስራ በመከናወኑ እንዲሁም ለባለሃብቱ ዝግ የነበሩ ሴክተሮችም ክፍት መደረጋቸው ለዘርፉ እድገትና ማንሰራራት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከፍተኛ እድገትና ማንሰራራት ላይ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
መድረኩ ጠንካራ ስራዎችን ለማጎልበት፣ ውስንነቶችን ለይተን በጋራ ለመቅረፍ እንዲሁም ሚናን ለይቶ ለመንቀሳቀስና ቅንጅታዊ አሰራርን ለመዘርጋት እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር በበኩላቸው ባለሃብቱንና የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በአግባቡ በመጠቀም፣ ምርቶችን በማስፋት ለገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን የማስገኘት ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የክልሉን ልማትና ሁለንተናዊ ብልጽግና ይበልጥ እውን ከማድረግ አኳያ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎችን በማጠናከር ወደ ክልሉ የሚመጡ አልሚ ባለሀብቶች በክልሉ ያለውን ሀብት ተጠቅመው መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የክልሉ መንግስት አስፈላጊ ድጋፎችን ያደርጋል ነው ያሉት።
በምክክር መድረኩ የፌዴራል፣ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የኢንቨትመንትና የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።