ቀጥታ፡

ሰልጣኞች በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀታቸው ዳብሯል

አርባምንጭ ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ):- የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የቴክኖሎጂ ዕውቀታቸውን እንዳዳበረው የአርባምንጭ ከተማ ሠልጣኞች ገለጹ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የአርባ ምንጭ ከተማ የኢትዮ-ኮደርስ ሰልጣኞች መካከል ወጣት ሊዲያ ዳሾ፤በአንድሮይድ ደቨሎፕመንት፣ ዳታ አናሊስስ፣ አርተፊሻል ኢንተለጀንስና ፕሮግራሚንግ ዘርፎች ስልጠና በመከታተል በአለም አቀፍ  ደረጃ  ተወዳዳሪ የሚያደርጋትን የምስክር ወረቀት መውሰዷን ገልጻለች።

ወቅቱ የሚጠይቀውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዕውቀት መያዝ  አስገዳጅ በመሆኑ ለዚሁ ራሷን ማብቃቷን አስረድታለች።


 

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የኦን ላይን ሥራዎችን ለመወዳደርና የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ ያለው መሆኑንም ተናግራለች፡፡

ሌላኛው ሠልጣኝ ወጣት ኦሳ ፋንታ በበኩሉ፤ በፕሮግራሚንግ እና ኮዲንግ ዘርፎች ስልጠና በመውሰድ የምስክር ወረቀት አግኝቷል።

ስልጠናው ወቅቱን የዋጀ የቴክኖሎጂ ክህሎት በማላበስ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን እንደሚጨምርለት ተናግሯል።


 

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መንግስት ወጪውን መሸፈኑ ዜጎችን ለማብቃትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የታለመ ትልቅ ዕድል ነው ብሏል።

የምስክር ወረቀቱ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው መሆኑ በየትኛውም ሀገር የሥራ እድልን ለማግኘት መሰረት እንደሚጥል  ገልጿል።

የአርባምንጭ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ በሃይሉ ካፒቴን ፤ መንግስት የዜጎችን የቴክኖሎጂ ዕውቀት ለማሳደግ የጀመረው  የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን  ተናግረዋል።


 

በተለይ ለወጣቶች  ዕውቀታቸውን በማሳደግ ለስራ ፈጠራ በማዋል ኢኮኖሚያዊ  ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና እንደ ሀገር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአርባምንጭ ከተማ 4 ሺህ 455 ዜጎች ስልጠና ወስደው የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም 4 ሺህ ዜጎችን ለማሠልጠን ግብ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን በእስካሁኑ 2 ሺህ 829 ዜጎች መሠልጠናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም